የኬንያ የምርጫ አፈጻጸም በሁሉም መመዘኛዎች ጥሩ የሚባል ነው - የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን
የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ “በምርጫው የፍትህ አካላት ሚና ከፍተኛ እንደነበር ተመክተናል” ብለዋል
ዶ/ር ሙላቱ ፤ አልፎ አልፎ የታዩት መስተጓጎል ለማስቀረት የምርጫ ቁሳቁስ አቅርቦትን በትክክል መፈጸሙን ማረጋገጥ እንደሚያሰፈልግ ተናግረዋል
ኬንያ ያካሄደችው ምርጫ ከዝግጅቱ ጀምሮ ጠንካራ የሚባልና የምርጫ አስተዳደር አፈጻጸሙ በሁሉም መመዘኛዎች የሚበረታታ ነው ሲል የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡድን ገለጸ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ናይሮቢ የደረሰውና በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የሚመራው የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን የኬንያ ምርጫን ቅድመ ዝግጅትና የምርጫ ሂደቱን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡
የታዛቢ ቡድኑ መሪ ዶ/ር ሙላት ተሾመ፤ የኬንያ የምርጫ እና የድንበር ጉዳዮች በሁሉም መመዘኛዎች ጥሩ ነው የሚባል የምርጫ ዝግጅት ማድረጉንና ምርጫ ማካሄዱን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ሙላቱ፤ ኬንያ ቀደም ሲል ባካሄደቻቸው ምርጫዎች፤ ከመራጮች ማንነት ማወቅና እና የውጤት ስርጭት ጋር በተያያዘ ይነሱ ነበሩ ችግሮች የሚቀርፍ ቴክኖሎጂ በዚህ ምርጫ ላይ ተግባራዊ መደረጉ እንዲሁም የሴቶችና ወጣቶች የምርጫ አስፈታሚዎች ውክልና መሻሻሉ በምርጫው ከታዘብናቸው በጎ እርምጃዎች ውስጥ ናቸውም ብለዋል፡፡
“የምርጫ ጣቢያዎችን አደረጃጀት እና የዳስ አቀማመጥ ፣ የድምጽ መስጫ ሚስጥራዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉና በየምርጫ ጣቢያው የሚኖሩ ረጃጅም ሰልፎች የሚያስቀሩ በቂ የዳስ ቤቶች መኖራቸው ታዛቢ ቡድኑ ከተመለከታቸውና ከተሻሻሉ ወሳኝ የምርጫ ዝግጅቶች መካከል ናቸው” ሲሉም አክለዋል፡፡
ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፤ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የታየውን አይነት መስተጓጎል ለማስቀረት የምርጫ ቁሳቁስ አቅርቦትን በትክክል መፈጸሙን በማረጋገጥ ረገድ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡
ከምርጫ አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማስተናገድ እና የህዝብን እምነት በማሳደግ እስከ ምርጫው ቀን ድረስ የፍትህ አካላት ሚና ከፍተኛ እንደነበርም ገልጸዋል የኢጋድ ታዛቢ ቡድን መሪው ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ።
ከተመለከትናቸው ጉዳዮች አንዱ በእጅ መመዝገቢያ አጠቃቀምን በተመለከተ የፍተህ አካላት የነበራቸው ሚና ነው ያሉት ዶ/ር ሙላቱ፤ በኬንያ ዲሞክራሲን ከማጠናከር አንጻር የኬንያ የፍትህ አካላት በህዝብ ያላቸውን ተአማኒነት እንደ ተጨባጭ ስኬት እንቆጥረዋለንም ብለዋል።
በመጨረሻም የኬንያ ህዝብ ምርጫው ሰላማዊ፣ ግልጽ እና ስርዓት ባለው መንገድ ለመሳተፍ ላሳየው ትዕግስት እና ቁርጠኝነት አመስግነዋል።
የኢጋድ ታዛቢ ቡድኑ ከቀጣናዊው ተቋም ስድስት አባል ሃገራት ማለትም ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከጅቡቲ፣ ከሶማሊያ እና ከኡጋንዳ የተውጣጡ ሰባት ዋና እና 24 ጊዜያዊ አባላት የተዋቀረ መሆኑ ይታወቃል፡፡