በዚህ ምርጫ ላይ 22 ሚሊየን ኬንያዊያን በመራጭነት ድምጽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል
ተጠባቂው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ነገ ይካሄዳል።
ኬንያን በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለመምራት የምረጡኝ ቅስቀሳቸው ሲያካሂዱ የነበሩ እጩ ፕሬዝዳንቶች ምርጫ ነገ እንደሚካሄድ ቢቢሲ ዘግቧል።
ኬንያን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት አራት እጩዎች የቀረቡ ሲሆን ባለፉት ምርጫዎች ላይ ለአራት ጊዜ ተወዳድረው ሽንፈትን ያስተናገዱት የኦሬንጅ ዲሞክራቲክ ሙቭመንቱ ራይላ ኦዲንጋ ዋነኛው ተፎካካሪ ናቸው፡፡
ራይላ ኦዲንጋ በፈረንጆቹ 1997 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገራቸውን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት እጩ የነበሩ ሲሆን በምርጫው ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡
በነዳጅ እና ሀይል ልማት ዘርፍ ነጋዴ የሖኑት የ77 ዓመቱ ኦዲንጋ ላለፉት አራት ተከታታይ ፕሬዝዳንታዊ የምርጫ ወቅቶች ላይ እጩ ቢሆኑም አብላጫ የህዝብ ድምጽ ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡
ውጤታቸውን ተከትሎም ራይላ ኦዲንጋ ከፕሬዝዳናታዊ ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸውን ከአምስት ዓመት በፊት ቢናገሩም ዘግይተው በሰጡት መግለጫ ለአምስተኛ ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት መልሰው እንደሚወዳደሩ አሳውቀዋል፡፡
ኬንያን አሁን ላይ በምክትል ፕሬዝዳንትነት እያገለገሉ ያሉት የዲሞክራቲክ ዩኒየኑ ዊሊያም ሩቶ ሌላኛው እጩ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ የራይላ ኦዲንጋ ዋነኛ ተፎካካሪ ናቸው ተብሏል፡፡
የ55 ዓመቱ ሩቶ ከፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በግጭት ውስጥ ሲሆኑ የጸባቸው መንስኤ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ለራይላ ኦዲንጋ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ከራይላ ኦዲንጋ እና ዊሊያም ሩቶ በተጨማሪ ለኬንያ ፕሬዝዳንትነት እየተፎካከሩት ያሉት ቀሪዎቹ እጩዎች ዳቪድ ዌሂጋ ጆርጅ ዋጃኮያህ ናቸው፡፡
የሬጌ ሙዚቃ ወዳጅ እንደሆኑ የሚናገሩት እጩ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዋጃኮያህ የብዙዎችን ትኩረት ስበዋል።
እጩ ፕሬዚዳንቱ በምርጡኝ ቅስቀሳቸው ላይ ማሪዋና የተሰኘው አደገኛ እጽ ማንኛውም አርሶ አደር እንዲያመርተው እና ምርቱን መጠቀም የፈለጉ ሁሉ በነጻነት እንዲጠቀሙት አደርጋለሁ፣ እንዲሁም ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ እንሲያስገኝ አደርጋለሁ ብለዋል።
የእባብ መርዝ በስፋት በማምረት ለኬንያ ዋነኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ መንገድ አደርጋለሁ ማለታቸው የብዙ ኬንያዊያንን ትኩረት እንዲስቡ ማድረጋቸውም ተገልጿል።
ኬንያን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት 55 እጩዎች ቀርበው የነበሩ ቢሆንም በመጨረሻም አራት ብቻ ቀርተዋል።
ኬንያን ላለፉት 10 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት የመሩት ኡሁሮ ኬንያታ የስልጣን ጊዜያቸውን ከሁለት ጊዜ በላይ ማራዘም ስለማይችሉ ለተመራጩ ፕሬዝዳንት እንዲያስረክቡ የሀገሪቱ ህገ መንግስት ያስገድዳቸዋል።