የሱዳን ተፋላሚዎች የጦር መሳሪያ ፋብሪካን ለመቆጣጠር ባደረጉት ውጊያ ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ ደረሰ
በሱዳን ግጭት ስምንተኛ ሳምንት የመሳሪያ ፋብሪካ ለመያዝ ውጊያ እየተደረገ ነው
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በጦር መሳሪያዎችና ጥይቶች የተሞላውን መጋዘን መያዙን አስታውቋል
የሱዳን ጦር ከተቀናቃኙ አንጃ ጋር ባደረገው ውጊያ ለሳምንታት ከባድ ጦርነት ሲካሄድበት የቆየውንና በደቡባዊ ካርቱም በሚገኘው የጦር መሳሪያ ፋብሪካ ከፍተኛ የእሳት አደጋ መከሰቱ ተነግሯል።
የሱዳን ግጭት በስምንተኛ ሳምንቱ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ማክሰኞ እለት ከፍተኛ ጥበቃ ያለውን ያርሙክ ወታደራዊ ሰፈርን ማጥቃቱን እማኞች ተናግረዋል።
ኃይሉ ረቡዕ እለት በጦር መሳሪያዎች እና ጥይቶች የተሞላውን መጋዘን እንዲሁም ወደ ስፍራው የሚወስዱ በርካታ የመግቢያ መንገዶች በቁጥጥሩ እንዳደረገ የሚገልጽ ምስል አውጥቷል።
ጦሩ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ግስጋሴን ለመመከት የአየር ድብደባ ተጠቅሟል ሲሉ እማኞች አክለዋል።
በሱዳን ትላልቅ ሶስት ከተሞች ካርቱም፣ባህሪ እና ኦምዱርማን በሁለቱ ተዋጊዎች መካከል ለ12 ቀናት የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደጋጋሚ ጥሰቶች በኋላ በመጠናቀቁ ውጊያው በርትቷል።
ጠዋት ላይ የጀመረው የእሳት አደጋ እሮብ ጀንበር ከመጥለቋ በፊት በድንገት መጠኑ እየጨመረ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የቃጠሎው መንስኤ በነዳጅ እና በጋዝ መጋዘኖች ላይ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ መሆኑንም ገልጸዋል።
ህዝባዊ አመጽ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽርን ከስልጣን ካስወገደ ከአራት ዓመታት በኋላ ሱዳን ወደ ሲቪል አገዛዝ የምታደርገው ሽግግር ዘግይቷል።