ወደ ሲቪል አገዛዝ ለመሸጋገር በወጣው እቅድ ምክንያት በተፈጠረው ውጥረት የሱዳን ተፋላሚዎች ወደ ግጭት ገብተዋል
በሱዳን የ24 ሰዓት የተኩስ አቁም ስምምነት ካበቃ በኋላ ውጊያው ቀጥሏል፡፡
በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ለ24 ሰዓት የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ከተጠናቀቀ በኋላ እሑድ ረፋድ ላይ ግጭት ተቀስቅሷል።
ስምንት ሳምንታት በደፈነው የሱዳን ግጭት በተቀናቃኝ ወታደራዊ አንጃዎች መካከል የተደረገው ጦርነት ለአጭር ጊዜ እንዲቆም ቢደረግም ከባድ ተኩስ ተሰምቷል።
የአይን እማኞች የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ሲያበቃ ግጭቱ መጀመሩን ተናግረዋል።
የኬንያው ፕሬዝዳንት የሱዳን ጄነራሎች “ይህን የማይረባ ጦርነት ሊያቆሙ ይገባል” ሲሉ አሳሰቡ
በሰሜን ኦምዱርማን፣ ካርቱም፣ ባህሪና ናይል ወንዝ ዙሪያ ጦርነቱ እንደገና መጀመሩን የዓይን እማኞቹ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በመዲናዋ ካርቱም ምስራቃዊ ዳርቻ ሻርክ ኤል-ኒል አካባቢ የመድፍ ተኩስ እንደነበር የተነገረ ሲሆን፤ ካርቱም ውስጥ ደግሞ ፍንዳታ እና ግጭት መከሰቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደገፈውና ወደ ሲቪል አገዛዝ ለመሸጋገር ከወጣው እቅድ ጋር በተገናኘ በተፈጠረው ውጥረት ምክንያት ነው።