ዶ/ር ወርቅነህ የኢትዮጵያ መሪዎች የተፈጠረውን ቁስል ለማከም ከፍተኛውን ሚና ሊጫወቱ ይገባል ብለዋል
በሰሜን ኢትዮጵያ ከ17 ወራት በፊት የተጀመረው ጦርነት መፍትሄ ያገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸው የኢጋድ ዋና ጸኃፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ዋና ጸኃፊው ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ ግጭት ሰላማዊ መፍትሄ የሚያገኝበት ተስፋ አለው ወይ ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ “አዎ፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ተስፋ ይታየኛል”የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ወርቅነህ(ዶ/ር) ፤ አሁን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ሆነ በሌሎች የጉዳዩ ተሳታፊ በሆኑ አካላት በኩል ያለው ቁርጠኝነት ተስፋ የሚሰጥ መሆኑንም ገልጿል፡፡
ዝርዝር ጉዳዮችንና አሁናዊ ሂደቶችን ከመግለጽ የተቆጠቡት ዋና ጸሃፊው “አሁንም ቢሆን ግጭቱ ቆሞ ሰለም እንዲመጣ በኢትዮጵያ መሪዎችና ህዝብ እምነት አለኝ፤ ምልክቶች የሚያሳዩትም እሱ ነው” ሲሉም ተናገሯል፡፡
የኢትዮጵያ መሪዎች የተፈጠረውን ቁስል ለማከም ከፍተኛውን ሚና ሊጫወቱ ይገባል ሲሉም አሳስቧል ዋና ጸሃፊው፡፡
ዋና ጸሀፊው ይህ ሀገር በርካታ ፈተናዎች፣ ችግርና ደስታ ያሳለፈ አብሮ ያሳለፈ ነው፤ እርግጥ ነው ግጭቶች ተከስተዋል፤ ከግጭት የሚያተርፍ ማንም የለም፤ ስለዚህም ግጭቱ በሰለማዊ መንገድ ነው መፈታት አለበት ብለዋል፡፡
የኢጋድ ዋና ጸኃፊ ዶ/ር ወርቅነህ ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ፤በኬንያ ሞምባሳ በተካሄደው ሁለተኛው የኢጋድ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ “ኢጋድ እንደ ተቋም በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ለመፍታት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ ነው” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ዋና ጸሃፊው “የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የጅቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ፣የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት፣ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፎርማጆ እንዲሁም አፍሪካ ህብረትና የተለያዩ አምባሳደሮች በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት መቋጫ እንዲያገኝ እያደረጉት ላለው ጥረት አደንቃለሁ” ሲሉ በወቅቱ ተናግረዋል፡፡
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በትግራይ፣አማራ እና አፋር ክልሎች መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ ማስከተሉ የሚታወቅ ነው፡፡በዚህ ጦርነት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ ለረሃብ ተጋልጠዋል እንዲሁም በርካቶች ሞተዋል፡፡
ግጭቱ በሰላም እንዲቋጭ ኢጋድን ጨምሮ ቀጣናዊ አለም አቀፍ ተቋማት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡
የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የሆኑት ኦባሳንጆ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖችን በማናገር ግጭቱን ለመፍታት በመጣር ላይ ናቸው፤ይህን ሂደት አሜሪካም ድጋፍ ሰጥታዋለች፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ ግጭት ማቆሙን ከገለጸ በኋላ የሰብአዊ እርዳታ በየብስ በኩል ወደ ትግራይ መግባቱን አለምአቀፉ የቀይ መስቀል ድርጅት ገልጿል፡፡
የኢጋድ ዋና ጸሃፊ በኤርትራ ጉዳይ
የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ(ዶ/ር) የኤርትራ ዳግም ወደ ኢጋድ አባልነት ለመመለስ ንግግር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዋና ጸሃፊው:“ኤርትራ ወደ ኢጋድ ልትመለስ የምርትችልበት ሁኔታ ይኖራል፤ንግግር እያደረግን ነው ያለነው” ብለዋል፡፡
ዶ/ር ወርቅነህ ይህን ይበሉ እንጂ መች እና እንዴት የሚለውን ዝርዝር ጉዳይ ከመናገር ተቆጥቧል፡፡“ወደ ፊት የምናየው ይሆናል” የሚል ጥቅል ምላሽም ሰጥቷል ዋና ጸሃፊው፡፡
በፈረንጆቹ 2007 ከምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) እራሷን ያገለለችው ኤርትራ እንደገና በ2011 ቡድኑን ተቀላቅላ በኢጋድ አባል ሀገራት በደረሰባት ተቃውሞ ለ2ኛ ጊዜ ከአባልነት መውጣቷ ይታወሳል።