የደቡብ ሱዳን መሪዎች ልዩነታቸውን አጥበው “ምናልባትም በዓለማችን ግዙፍ የሚባል መንግስት መመስረት ችለዋል”- አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን
ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ለደቡብ ሱዳን የሽግግር ስምምነት ተግባራዊነት ቁርጠኛ አመራር እየሰጡ ነው
ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲመጣ የሰራው ስራ በታሪኩ ትልቅ ስኬት ተብሎ የሚጻፍለት መሆኑንም አሰታውቀዋል
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲመጣ የሰራው ስራ በታሪኩ ትልቅ ስኬት ተብሎ የሚጻፍለት መሆኑን በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን ገለጹ።
አምባሳደሩ የደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታን በማስመልከት ከአል-ዐይን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ “ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ሰላም እንደሚጣ ያደረገው ጥረት ደቡብ ሱዳናውያን በታሪካ የማይዘነጉት ትልቅ ስኬት ነው” ብለዋል።
“እንደፈረንጆቹ 2005 በናይሮቢ ኬንያ የተፈረመው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት እንዲሁም ደቡብ ሱዳን በ2011 ነጻነቷን መቀዳጀቷን ተከትሎ በ2013 የተቀሰቀሰው የውስጥ ችግር ሰላማዊ መፍትሄ እንዲኖረው በ2018 የተደረሰው ስምምነት ኢጋድ ለደቡብ ሱዳን ሰላም ካደረገው ጥረትና ካሳካቸው ስኬቶች የሚጠቀሱ ታሪካዊ ምእራፎች ናቸው” ሲሉም አምባሳደሩ በአብነት አንስቷል።
ኢጋድ ባለፈው ወረሃ ታህሳስ በኬንያ ሞምባሳ ባካሄደው ሁለተኛ ዓመታዊ ስብሰባው በደቡብ ሱዳን የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ከሀገሪቱ መንግስት ጋር እየሰራ መሆኑን ዋና ጸሃፊው ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ መናገራቸው ይታወሳል።
የደቡብ ሱዳን አመራሮች ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ያሉት ዋና ጸሃፊው፤ የስምምነቱ ተግባራዊነት የተሟላ የሚሆነው በፀጥታ መወቅሩ የሚደረገውን ስብጥር እውን ማድረግ ሲቻል እንደሆነ መናገራቸውም አይዘነጋም።
የኢጋድ ዋና ጸሃፊው ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ሃሳብ በመንተራስ “የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ” በደቡብ ሱዳን መንግስት በኩል ያለ ቁርጠኝነትን በተመለከተ ከአል-ዐይን ኒውስ ለቀረበላቸው ጥያቄም አምባሳደሩ ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚህም ደቡብ ሱዳን በርካታ ፈታናዎች ያሏት ሀገር ብትሆንም ፈተናዎችን ተሻግራ “ቶክስ ማቆም” ችላለች ያሉት አምባሳደሩ፤ በቀጣይ በተደረሰው ስምምነት መሰረት የተቀሩትን የሽግግሩ ስምምነቶች እውን ለማድረግ በመንግስት በኩል እየተሰራ መሆኑን አመላክቷል።
የደቡብ ሱዳን መሪዎች የነበራቸውን ልዩነት አጥብበው አሁን ላይ “ምናልባትም በዓለማችን ግዙፍ የሚባል መንግስት መመስረት ችለዋል” ብለዋል አምባሳደሩ።
በተደረሰው ስምምነት መሰረት “5 ምክትል ፕሬዝዳንቶች፣ 1 ሺህ የሚሆኑ እንደራሴዎች፣ እንዲሁም በርካታ የክልል መንግስታት” መዋቀራቸውን ያነሱት አምባሳደሩ፤ የተቀረውን የጸጥታ መዋቅሩ ስብጥር እውን የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆንና “ኢጋድ በዚህ ሃሳብ ሊገባው እንደማይገባ”ም አረጋግጧል።
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ለሽግግር ስምምነቱ ተግባራዊነት ቁርጠኛ አመራር እየሰጡ እንደሆነም ጭምር ተናግሯል፡፡
አምባሳደሩ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሚናን በተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸው “ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰላም ስምምነቱ ባይሳካ ደስ የሚለው ይመስላል” ሲሉ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ የደቡብ ሱዳን ህዝብ “የዓለም መሳቅያ ላለመሆን” የሽግግር ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ ነው ብለዋል።
እንደፈረንጆቹ 2013 በደቡብ ሱዳን በተፈጠረው ቀውስ እንዲሁም በመንከባለል ላይ ባለውና ያልተቋጨ ስምምነት ምክንያት ፤ አዲስቷ ሀገር በተጠበቀችው ልክ ለውጥ እንዳታመጣ ወደ ኋላ እንደጎተታት እስካሁን መዝለቁ ይታወቃል።