“ደቡብ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ፊቷን የምታዞርበት ምንም ምክንያት የለም”- አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን
አምባሳደር ጀምስ በቅርቡ “የደቡብ ሱዳንን ፍላጎትና አቋም” በማይገልጽ መልኩ ዘገባ ባቀረቡ መገናኛ ብዙሃን ማዘናቸውን ገልፀዋል
ኢትዮጵያ ከፈቀደች ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር የኢትዮጵያን ጉዳይ በሰላም እንዲያልቅ የማገዝ ፍላጎት እንዳላቸውም አስታውቀዋል
ደቡብ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ፊቷን የምታዞርበት ምንም ምክንያት የለም ሲሉ በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን ተናገሩ።
አምባሳደሩ ይህንን ያሉት የኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ትብብር እንዲሁም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የደቡብ ሱዳን ምልከታና አቋምን በተመለከተ ከአል-ዐይን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው።
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የቆየና ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው ያሉት አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን፤ አሁን ላይ በተለያዩ የትብብር ማእቀፎች ከስምምነት ላይ በመድረስ በጋራ እየሰሩ መሆናቸው ገልጸዋል።
እንደፈረንጆቹ 2018 በሀገራቱ መካከል በተደረሰ ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን በፓለቲካዊ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰሩ ይገኛሉም ብለዋል።
አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን እሳቸውን ዋቢ በማድረግ በቅርቡ “የህወሀት ኃይል ከደቡብ ሱዳን ጋር ግንኙነት እንዳለው” ተደርጎ በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የቀረበው ዘገባ ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል።
ዘገባው በደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር የሚመራው ተቃዋሚ ኃይል ከህወሀት ጋር ግንኙነት እንዳለው ተደርጎ መቅረቡ የሚታወስ ነው።
አምባሳደሩ የደቡብ ሱዳንን ፍላጎትና አቋም በማይገልጽ መልኩ ዘገባውን ባቀረቡት መገናኛ ብዙሃን ማዘናቸውም አስታውቀወል።
አሁን ላይ በሱዳን የሚገኙ ተቃዋሚ ኃይሎች የሱዳን መንግስት እንደሆኑና በኢትዮጵያ ጉዳይ “የመንግስት አቋም ከማራመድ ውጭ ሌላ አቋም የሚያራምዱበት ምክንያት የለም” ሲሉም አምባሳደሩ አስረድተዋል።
በፕሬዝዳንት ሳልቫኪር የሚመራው የሱዳን መንግስት ፍላጎት በኢትዮጵያ ሰላም እና ብልጽግና ተረጋግጦ ማየት ነው ያሉት አምባሳደር ጀምስ፤ የተቀዳሚ ም/ፕሬዝዳንት ማቻር ፍላጎትም ተመሳሳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጉዳይ የውስጥ ጉዳይ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጣልቃ ገብነትን እንደማይፈቅድም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ወዳጅ እንደመሆኗ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር እድል ካገኙ የኢትዮጵያን ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ እንዲያልቅ ፍላጎት እንዳላቸውም አምባሳደሩ አስረድተዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን የተባለ ነገር እንደሌለ እና ደቡብ ሱዳን ምላሽ እየጠበቀች መሆኗንም ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያ የውስጧን ችግር የመፍታት አቅም እንዳላት እናምናለን፤ ይሁን እንጅ አውንታዊ ምላሽ ከተሰጠ የድርሻችን እገዛ የምናደረግ ይሆናል”ም ነው ያሉት አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን።
ኢትዮጵያ የቀጠናው መሪ እንደመሆኗ፤ ሰላም የሰፈነባት እና የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን እንድትሆነ ደቡብ ሱዳን አስፈላጊውን እገዛ የማድረግ ኃላፊነት አለባትም ብለዋል።
ሚድያዎች አሁን ካለው የኢትዮጵያ ሁኔታ በተጨማሪ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ደቡብ ሱዳን ከግብጽ ጋር እንደምትተባበር አድረገው በተለያዩ ጊዜያት መሰረተ ቢስ የሆኑ ዘገባዎች ሲዘግቡ መቆየጣቸው ያስታወሱት አምባሳደሩ “ደቡብ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ፊፏን የምታዞርበት አንዳችም ምክንያት የላትም” ሲሉም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን እንደፈረንጆቹ 1972 (የደቡብ ሱዳን የነጻነት ትግል ከተጀመረበት ወቅት) የጀመረ ታሪካዊ ግንኙነት ያለቸው ሀገራት መሆናቸው ይታወቃል።