የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ (SPLM/A-IO) ቡድኖች ተኩስ ለማቆም መስማማታቸው ተገለጸ
በጀነራል ሲሞን የሚመራው ክንፍ ሪክ ማቻር የፓርቲው መሪ አለመሆናቸውን ማወጁ ለግጭቱ መንስኤ ነበር
ኢጋድ አመራሮቹ ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ከቀናት በፊት ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል
የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ቡዱኖች ባለፈው ሳምንት የጀመሩትንና የ34 ወታደሮች ህይወት የቀጠፈውን ግጭት ለማቆም ከስምምነት መድረሳቸው ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
የኤስፒኤልኤም የኢንፎርሜሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ፕዋክ ባልዋንግ በደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር የሚመራው ቡድን እና በጀነራል ሲሞን የሚመራው ቡድን ከስምምነት መድረሳቸውን አስተዋቋል፡፡
“በጀነራል ሲሞን የሚመራውና ራሱን ኪትግዋንግ ዲክሌሬሽን ብሎ የሚጠራው ቡድን የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንደሚቀበል እንዲሁም ማቻር የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚፈልጉ ሁለቱም ቡዱኖች የማስታረቅ ሚና እየተጫወቱ ላሉት ጀነራል ጆንሰን ኦሎኒ ገለጸውላቸዋል”ም ነው ያሉት ፕዋክ ባልዋንግ ፡፡
በደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር በሚመራው ኤስፒኤልኤም አይ ኦ (SPLM/A-IO) ፓርቲ ውስጥ ባለፈው ሳምንት ክፍፍል መፈጠሩ የሚታወስ ነው፡፡
በፓርቲው ውስጥ ተፈጥሯል በተባለው ክፍፍልም በሪክ ማቻር የሚመራ እና በጀነራል ሲሞን የሚመሩ ወታደሮች እንዳሉ ይፋ ተደርጓል፡፡
ተኩሱ የተከፈተውም ሪክ ማቻርን የአመራር ክፍትት አለባቸው እንዲሁም በሙስና ተዘፍቀዋል በሚል ከኤስፒኤልኤም አይ ኦ ፓርቲ መሪነት ለማውረድ ሙከራ ከተደረገ ከሶስት ቀናት በኋላ ነው፡፡
በፓርቲው ውስጥ አፈንጋጭ እንደሆነ የተገለጸው እና በጀነራል ሲሞን የሚመራው ክንፍ ሪክ ማቻር የፓርቲው መሪ አለመሆናቸውን ማወጃቸውንም የሚታወቅ ነው፡፡
ጀነራል ሲሞን፤ ከዚህ በኋላም ሪክ ማቻር ይመሩት የነበረው ኤስፒኤልኤም አይ ኦ ፓርቲ መሪ እኔ ነኝ ማለታቸውን የተገለጸ ሲሆን ለእርሳቸው ታማኝ የሆኑ ኃይሎችም በማቻር ወታደሮች ላይ ተኩስ መክፈታቸው ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
ለሪክ ማቻር ታማኝ ሆኑት የፓርቲው ቃል አቀባይ ላም ፉል ጋብርኤል በጁባ ከተማ ለአል ዐይን ኒውስ በሰጡት ቃለ ምልልስ በጀነራል ሲሞን የሚመሩ ወታደሮች በካይዛን አካባቢ ተኩስ መክፈታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ጀነራል ሲሞን የፓርቲው መሪ መሆናቸውን የገለጹት ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን በሚዋሰኑበት ሙጋይን አካባቢ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት/ኢጋድ/ ዋና ጸሃፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የደቡብ ሱዳኑ ነጻ አውጭ ንቅናቄ አንጃዎች አመራሮች ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ከቀናት በፊት ጥሪ ማቅረባቸው ሚታወስ ነው፡፡