“ዛሬም ወደፊትም ከደቡብ ሱዳን የሚመጣ ኢትዮጵያን ሊጎዳ የሚችል ነገር የለም”- ሪክ ማቻር
ማቻር “ጠንካራ” ያሉትን በየጊዜው የነበሩ የኢትዮጵያ መንግስታት ቁርጠኝነትን አድንቀዋል
ማቻር በጁባ ከኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል መሃዲ ጋር ተወያተዋል
የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር (ዶ/ር) “ዛሬም ወደፊትም ከደቡብ ሱዳን የሚመጣ ኢትዮጵያን ሊጎዳ የሚችል ነገር የለም”ሲሉ ተናገሩ፡፡
ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንቱ በጁባ ከኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል መሃዲ ጋር ተገናኝተው መምከራቸውን ኤምባሲው አስታውቋል፡፡
በምክክሩ የሃገራቱን የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ያነሱት ማቻር “ጠንካራ” ያሉትን በየጊዜው የነበሩ የኢትዮጵያ መንግስታት ቁርጠኝነትን አድንቀዋል፡፡
ሪክ ማቻር “ደቡብ ሱዳን” የሚለው ስም እንዲቀየር ሃሳብ አቀረቡ
ደቡብ ሱዳን ለኢትዮጵያ ሰላም ስላላት ቁርጠኝነት አስምረው የተናገሩም ሲሆን “ዛሬም ሆነ ወደፊት ከደቡብ ሱዳን የሚመጣ ኢትዮጵያን ሊጎዳ የሚችል ነገር የለም” ብለዋል።
አምባሳደር ነቢል በበኩላቸው ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታዎችን በተመለከተ ለተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
በጦር ግንባር ስላሉ ለውጦች፣ ስለ ሰብዓዊ የእርዳታ ጥረቶች፣ በሽብርተኝነት በተፈረጀው የህወሓት ኃይል ስለተፈጸሙ ዘግናኝ ግፎች እና ቡድኑ ስለፈጠራቸው ሰብዓዊ ድቀቶች ማብራራታቸውንም ኤምባሲው አስታውቋል፡፡
በምዕራባዊ ብዙሃን መገናኛዎች ስለ ተፈጸሙ ሚዛናዊነት የጎደላቸው ዘገባዎች እንዳስረዱም ነው የገለጸው፡፡
“ደቡብ ሱዳን መሬቶቿ ኢትዮጵያን ለመጉዳት እንዲውሉ አትፈቅድም”- የደቡብ ሱዳን የሃገር ግዛት ሚኒስትር
“በሰሞኑ ወታደራዊ ኦፕሬሽን የተደናገጠው ህወሓት የጎረቤት ሀገራት ተቃዋሚዎችን ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ ውስጥ መግባቱን ምንጮቼ ገልጸውልኛል” የሚል ዘገባን የሰራው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሪክ ማቻር ሰዎች የሕወሓትን ሰዎች ለማስታጠቅና ወደ ጋምቤላ ለማስገባት በጁባ መምከራቸው ተደርሶበታል ማለቱ የሚታወስ ነው፡፡
አንዳንድ የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት በጉዳዩ እንዳሉበት ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ በመግለጽ ማቻር የት እንዳሉ እንደማይታወቅ መዘገቡም አይዘነጋም።