ኢጋድ፤ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጋለጡ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የተሻለ “የዘር ፖሊሲ” ያስፈልጋቸዋል አለ
ዶ/ር ሞህይልዲን ኢልቶሃሚ፤ በቀጠና ደረጃ “ድንበር ተሻጋሪ የሰብል ዘር ግብይት” እንዲኖር እንሰራለን ብለዋል
የአፍሪካ ቀንድ “የተሻሻለና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ዘር ያስፈልገዋል” ተብሏል
ለከፍተኛ የምግብ እጥረት በተጋለጡት የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ያለውን ችግር ለማቃለል የተሻለ “የዘር ፖሊሲ” እንደሚያስፈልግ የኢጋድ ሪጅናል ሲድ ዳያሎግ ፎረም ጠቆመ፡፡
ፎረሙ ይህን ያመላከተው የኢጋድ አባል ሀገራት ተወካዮች እንዲሁም የተላያዩ ባለድርሻ አካላት ባሳተፈውና ላላፉት ሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡
ዘር የሰብል ምርት መሰረታዊ እንዲሁም የሰብል ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል ቁልፍ ግብአት ቢሆንም፤ ጥራት ያለው ዘር የማግኘት እና የገበሬዎች የተሻሻሉ ዝርያዎችን ከመጠቀም አንጻር ከሰሃራ በታች ባሉ በርካታ ሀገራት ዝቅተኛ መሆኑ በፎረሙ ተመላክቷል፡፡
በጉዳዩ ላይ ከአል-ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢጋድ የእርሻና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ኃላፊ ዶ/ር ሞህይልዲን ኢልቶሃሚ አፍሪካ ቀንድ ከተለመዱ ዘሮች በዘለለ የተሻሻሉ የዘር አማራጮች ለመጠቀም የሚያችላቸው የዘር ፖሊሲ /Seed Policy/ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ እንደ በቆሎ ማሽላ፣ ስንዴ፣ ጤፍ እና ገብስ የመሰሳሰሉ የተለያዩ የመኖ የሰብል ዝርያዎች በአፍሪካ ቀንደ ማየት የተለመድ ነው ያሉት ኃለፊው፤ያም ሆኖ የቀጠናው የግብርና አቅም ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖዎች የተጋለጠ መሆኑ አንስተዋል፡፡
“የአፍሪካ ቀንድ የተሻሻለ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ዘር ያስፈልገዋል”ም ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሞህይልዲን ኢልቶሃሚ፤ ሁሉም የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ አባል ሀገራት ያላቸውን የዘር ፖሊሲ ማሻሻል ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የሪጅናል ሲድ ዳያሎግ ፎረም ዋና ዓላማ አባል ሀገራት በሰብል ምርት፣ በዘር አመራረት ፣ በዘር ግብይት እና በፖሊሲ ማሻሻያ ዘርፎች ያላቸውን መልካም የሚባል ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ መሆኑም ተናግረዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር፤ በሀገራት መካከል የዘር ግብይት/Seed Trade/ እውን የማድረግ የፎረሙ ዐቢይ አላማ ነው ብለዋል፡፡
ፎረሙ “በቀጣና ደራጃ ያሉትን የዘር ፖሊሲዎችን በማጠናከር ድንበር ተሻጋሪ የዘር ግብይት እንዲኖር የማድረግ አላማ አለው”ም ነው ያሉት ዶ/ር ሞህይልዲን ኢልቶሃሚ፡፡
በመስራቅ አፍሪካ 50 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የምግብ ዋስትና እንደሚያስፈልጋቸው የምስራቅ አፍሩካ በይነ መንግስታት/ኢጋድ/ ሪፖርት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ይፋ መድረጉ አይዘነጋም፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ እንደ ኬንያ፣ሶማሊያ፣ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን ለከፍተኛ የምግብ ቀውስ የገጠማቸው የቀጠናው ሀገራት መሆናቸውም ጠቅሷል፡፡
ለተከሰተው የምግብ እጥረት በቀጣናው የተከሰተው ተደጋጋሚ ድርቅ፣ ጎርፍ እና ሌሎች ከአየር ንብረት ጋር የተገናኙ አደጋዎች ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ የገለጸው ሪፖርቱ፤ የቀጣናው ሀገራት በዓለም ላይ እየተከሰቱ ያሉ ተለዋዋጭ ተጽእኖዎችን መቋቋም የሚያስችሉ እቅዶችን ተግባራዊ ማድረግ እንሚጠበቅባቸውም ጠቁሟል፡፡