ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የምግብ ቀውስ ገጥሟቸዋል - ኢጋድ
ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ “በቀጠናው ባለፉት 4 አስርት ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ ተከስቷል” ብለዋል
በ2022 በሶማሊያ እና በደቡብ ሱዳን ብቻ 300 ሺህ ሰዎች ለረሃብ አደጋ እንደሚጋለጡ የኢጋድ ሪፖርት አመላክቷል
ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የሆነ የምግብ ቀውስ እንዳጋጠማቸው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ገለጸ፡፡
የኢጋድ አባል ሀገራት ድርቅን ለመቋቋምና በዘላቂነት ለመከላከል እያከናወኑት ያለው የእቅድ ትግበራ ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት የተደገበት ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
ውይይቱን ተከትሎ የወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነ፤ ምስራቅ አፍሪካ ለከባድ የምግብ ቀውስ ተጋልጧል እንዲሁም ያለው ቀውስ በከፍተኛ መጠን የመባባስ እድሉ ሰፊ ነው፡፡
በምሰራቅ አፍሪካ 50 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ለከፍተኛ የምግብ ቀውስ መጋለጣቸው ያመላከተው ሪፖርቱ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ እንደ ኬንያ፣ሶማሊያ፣ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን ለከፍተኛ የምግብ ቀውስ የገጠማቸው የቀጠናው ሀገራት መሆናቸውም ጠቅሷል፡፡
በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት 2022 በሶማሊያ እና በደቡብ ሱዳን ብቻ ወደ 300 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች የረሃብ አደጋ ሊገጥማቸው እንደሚችልም ሪፖርቱ አሳስቧል፡፡ለችግሩ ዋና ተጋላጭ ከሆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት መሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡
በተወካያቸው አማካኝነት በጉባኤው መልዕክት ያስተላለፉት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ዋና ጸሃፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ፤ በቀጠናው ባለፉት 4 አስርት ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ መከሰቱንና በዚህም በቀጠናው የምግብ ዋስትና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ “ዛሬ ይፋ የምናደርጋቸው አሃዞች ልብ የሚሰብሩ ናቸው፣ እና ከጥቅምት እስከ ታህሳስ ያለው የዝናብ ወቅት ደካማ በመሆኑ የበለጠ እንዳይጨምሩ እጨነቃለሁ”ም ብለዋል፡፡
የኢጋድ አባል ሀገራት ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ “በዓለም ላይ እየተከሰቱ ያሉ ተለዋዋጭ ተጽእኖዎችን መቋቋም የሚያስችሉ እቅዶችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል”ም ነው ያሉት ዋና ጸሃፊው፡፡
"በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ (ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ) ያለው የምግብ ዋስትና ሁኔታ አራት ተከታታይ ዝናባማ ወቅቶች ካለምንም ዝናብ ካለፉ በኋላ፣ የአየር ንብረት ሁኔታ ቢያንስ በ40 ዓመታት ውስጥ ያልታየና በጣም አሳሳቢ ሆኗል" ያሉት ደግሞ የኤፍኤኦ የምስራቅ አፍሪካ ንዑስ ክፍል አስተባባሪ ዶ/ር ቺሚምባ ዴቪድ ፒሪ ናቸው፡፡
"አሁን ከምንጊዜውም በላይ በቀጠናችን የምግብ ቀውሶች መንስኤዎችን ለመፍታት ያለመ የአጭር ጊዜ ኑሮ ቆጣቢ ምላሾችን በረጅም ጊዜ የመቋቋም አቅም ግንባታ መተግበር አለብን" ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
የኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያ እና አፕሊኬሽንስ ሴንተር (ICPAC) የቅርብ ጊዜ ትንበያ በቀጠናው ለአምስተኛ ተከታታይ ጊዜ ያልተሳካ የዝናብ ወቅት እንደሚኖር ጠቁሟል፡፡
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ማይክል ደንፎርድ በበኩላቸው “ግጭት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ዋጋ መጨመር እንዲሁም አሁን በዩክሬን ያለው ግጭት በምግብ እና በሃይል ዋጋ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በምስራቅ አፍሪካ ለረሃብ እየዳረገ ነው” ብለዋል።
በአሳዛኝ ሁኔታ በቀጠናው ውስጥ በጣም ትክክለኛ የሆነ የረሃብ አደጋ አለ ያሉት ማይክል ደንፎርድ፤ ይህ እንዳይከሰት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ወደፊት ለሚፈጠሩ ቀውሶች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም መገንባት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።