ኢጋድ በምሰራቅ አፍሪካ 50 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የምግብ ዋስትና ያስፈልጋቸዋል አለ
በቀጠናው ባለፉት 4 አስርት ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ ተከስቷል ብሏል ኢጋድ
የድርቅ አደጋን መቋቋም ላይ ትኩረቱን ያደረገው የኢጋድ ጉባኤ በነገው ዕለት በአዲስ አበባ የሚካሄድ ይሆናል
በምሰራቅ አፍሪካ 50 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የምግብ ዋስትና እንደሚያስፈልጋቸው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ዋና ጸሃፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ተናገሩ፡፡
ዋና ጸሃፊው ይህን ያሉት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለውና የድርቅ አደጋን መቋቋምና በዘላቂነት መከላከል ላይ ትኩረቱን አድርጎ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ አካል በሆነው፤ የኢጋድ 14ኛው የአስተባባሪ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ነው፡፡
ዋና ጸሃፊው በስብሰባው ባደረጉት ንግግር ኢጋድ በቀጠናው ያሉ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ድርቅን የመቋቋም አቅማቸውን ለማጠናከር ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።
በቀጠናው ባለፉት 4 አስርት ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ መከሰቱን የገለጹት ዋና ጸሃፊው፤ በዚህም በቀጠናው የምግብ ዋስትና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተናገርዋል፡፡
“አሁን ላይ በቀጣናው 50 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የምግብ ዋስትና ያስፈልጋቸዋል”ም ብለዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አባል ሀገራት ወቅታዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተፈጥሮአዊና
“የቀጣናው ሀገራት በዓለም ላይ እየተከሰቱ ያሉ ተለዋዋጭ ተጽእኖዎችን መቋቋም የሚያስችሉ እቅዶችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል” ሲሉም አክለዋል።
በቀጣናው የተከሰተው ተደጋጋሚ ድርቅ፣ ጎርፍ እና ሌሎች ከአየር ንብረት ጋር የተገናኙ አደጋዎች በማህበረሰቡ ኑሮ ላይ ተጽእኖ ፈጥረዋል ያሉት ደግሞ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ፍቅሩ ረጋሳ ናቸው፡፡
ሚኒስትሩ ችግሩን ከግምት በማስገባት ኢትዮጵያ ችግሩን መቋቋም የሚያስችል የአቅም ግንባታ ፕሮጀክቶችን ቀርጻ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ናትም ብለዋል፡፡
ተጽዕኖውን በዘላቂነት ለመቋቋም የተቀናጀ ሁሉን አቀፍ የልማት ጥረቶች እንደሚያስፈልጉም ተናግረዋል፡፡
ውሃና የእንስሳት መኖ ልማት እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
የድርቅ አደጋን መቋቋም ላይ ትኩረቱን አድርጎ በነገው ዕለት በአዲስ አበባ በሚካሄደው የኢጋድ ጉባኤ የአባል ሀገራቱ ሚኒስትሮች ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ጉባኤው በዋናነት ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ፣የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ያስከተለው ተጽእኖ ላይ ምክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በጉባኤው የኢጋድ አባል ሀገራት ድርቅን ለመቋቋምና በዘላቂነት ለመከላከል እያከናወኑት ያለው የእቅድ ትግበራ ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡