የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች የሰላም ስምምነቱን ለመተግበር “ግልጽ የሆነ የጊዜ ሰሌዳ ሊኖራቸው” እንደሚገባ ኢጋድ አሳሰበ
ኢጋድ የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የወሰደውን አዎንታዊ እርምጃ አድንቋል
39ኛው የኢጋድ የመሪዎች ስብሰባ በናይሮቢ ተካሂዷል
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት የልማት ባለስልጣን (ኢጋድ) የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለመተግበር ግልጽ የሆነ የጊዜ ሰሌዳ ሊኖራቸው ይገባል አለ፡፡
39ኛው የኢጋድ የመሪዎች ስብሰባ በናይሮቢ ተካሂዷል፡፡ ጉባኤው በተለያዩ አንኳር ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደመከረም ያስታወቁት የኢጋድ ቃል አቀባይ ኑር መሃመድ ሼክ በደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ መወያየቱን ገልጸዋል፡፡
እንደ ቃል አቀባዩ ከሆነ፤ ኢጋድ እንደፈረንጆቹ በ2018 የተደረሰውን የሰላም ስምምነትን ተከትሎ እስካሁን የተገኘውን እድገትና ያለው አፈጻጸም አድንቋል፡፡
“ኢጋድ የብሔራዊ አንድነት እና ፓርቲዎች የሽግግር መንግስት የምርጫ አፈጻጸምን ጨምሮ ቀሪ ተግባራትን ለማጠናቀቅ ግልጽ የሆኑ መለኪያዎች ተጨባጭ የጊዜ ሰሌዳዎችን እና ፍኖተ ካርታ እንዲያዘጋጁ ጥሪ አቅርቧል” ሲሉም አክለዋል።
ኢጋድ ከደቡብ ሱዳን በተጨማሪ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አንስቶ ተወያየ ሲሆን፤ መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ላይ ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የወሰደውን አዎንታዊ እርምጃ አድንቋል።
በቀጠናው ያለው የሰብአዊ እና የጤና ሁኔታ አሳሳቢ ነው ያለው ኢጋድ፤ ዓለም አቀፍ አጋሮች የሰብአዊ እርዳታን መጠን በአስቸኳይ እንዲያሳድጉ ሲል መጠየቁንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ሌላው ቀጠናው በርካታና ተለዋዋጭ የጸጥታ፣ ማህበረ-ኢኮሚያዊ ለውጦች እየተስተዋሉ መሆናቸውና እነዚህን ለውጦች በትኩረት በማጤን መፍትሄዎች ማበጀት እንደሚገባም የኢጋድ የመሪዎች ስብሰባ ትኩረት ሰጥቶ መክሯል፡፡
ኢጋድ በፖለቲካ ሽግግር ዙሪያ በሚያደርገው ጥረት እና ጽንፈኝነትን በመዋጋት ረገድ በሚጫወተው ሚና የአፍሪካ ህብረት ድጋፍ አይነተኛ ነው ማለቱም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡