ደቡብ ሱዳን ሱዳናዊያንን ማደራደር እንደምትፈልግ አስታወቀች
ፕሬዘዳንት ሳልቫኪር የሱዳን ወታደራዊ እና ሲቪል አስተዳድሩ መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለማጠበብ ማደራደር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል
ድርድሩን ለመጀመርም ወደ ካርቱም የመጀመሪያ ልዑካቸውን ልከዋል
ደቡብ ሱዳን ሱዳናዊያንን ማደራደር እንደምትፈልግ አስታወቀች፡፡
በሱዳን ከአንድ ሳምንት በፊት ወታደራዊ አመራሩ በሲቪል አስተዳድሩ ላይ በፈጸመው መፈንቅለ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በርካታ አመራሮች በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
በሱዳን ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል አልቡርሀን የሚመራው የሱዳን ጦር የሲቪል አስተዳድር አፍርሰው በወታደራዊ አመራሩ የሚመራ የአስቸኳይ ጊዝ አዋጅ ማወጃቸውን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ድርጊቱን አሜሪካን እና አውሮፓ ህብረትን ጨምሮ በርካታ አገራት እና ተቋማት ከማውገዛቸው በተጨማሪ ወታደራዊ አመራሩ ስልጣኑን ለሲቪል አሰተዳድሩ እንዲያስረክብ በመወትወት ላይ ናቸው፡፡
የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዘዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ወደ ግጭት የገቡ ሱዳናዊያንን ለማደራደር እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል፡፡ ወደ ግጭት የገቡት የሱዳን ወታደራዊ እና ሲቪል አስተዳድር አመራሮች ለድርድር ዝግጁነታቸውን ለመጠየቅም በደህንነት አማካሪያቸው ቱት ጋልዋክ የሚመራ ለኡክ ወደ ካርቱም ልከዋል፡፡
ይህ ልኡክም ከሱዳን ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል አልቡርሃን ጋር የተወያየ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ በእስር ላይ ካሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብደላ ሀምዶክ እና ሌሎች አመራሮች ጋር እንደሚወያይ በካርቱም ያለው የአልአይን ዘጋቢ ጠቅሷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክና የሲቪል መንግስቱ ባለስልጣናትን ከስልጣን ያነሱት የሱዳን ጦር አዛዥ አል ቡርሃን በሀገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህ ባለፈም፤ አል ቡርሃን በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ህብረት እና በፈረንሳይ የሚገኙትን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት የሚገኙ የሱዳን አምባሳደሮችን ከስራ ማባረራቸው አይዘነጋም፡፡
ዲፕሎማቶቹ የሱዳን የሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አብደላ ሃምዶክን በመደገፋቸው ከኃላፊነት መነሳታቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡