በሱዳን መረጋጋት እስከሚፈጠር ድረስ ነዳጅ በፖርት ሱዳን በኩል እንደማትልክም ገልጻለች
ደቡብ ሱዳን ፖርት ሱዳንን በመጠቀም ነዳጅ ወደ ውጭ ሀገራት መላክ ማቆሟን አስታወቀች።
የደቡብ ሱዳን ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሚካኤል ሉዌት ለአል ዐይን ኑውስ እንዳሉት፤ ነዳጅ የማውጣቱ ስራ እንደቀጠለ ቢሆንም በፖርት ሱዳን በኩል ለዓለም ገበያ የመላኩ ስራ ግን ቆሟል ብለዋል።
በሱዳን መፈንቅለ መንግስት መከሰቱን ተከትሎ የፖለቲካ አለመረጋጋት መፈጠሩ ደቡብ ሱዳን ነዳጅ በፖርት ሱዳን ወደብ እንደማይላክ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
በሱዳን የተከሰተው የፖለቲካ ውጥረት ሱዳን የውስጥ ጉዳይ ቢሆንም ክስተቱ የአካባቢውን ንግድ እየጎዳ መሆኑንም ቃል አቀባዩ ገለጸዋል።
ሱዳን ወደ መረጋጋት ስትመለስ ደቡብ ሱዳን ነዳጅ በፖርት ሱዳን በኩል መላኳን እንደምትጀምር የተናገሩት ቃል አቀባዩ መረጋጋቱ መቼ ሊመጣ እንደሚችል አሁን ላይ መናገር እንደማይቻልም አክለዋል።
ደቡብ ሱዳን ኢኮኖሚዋ በነዳጅ ንግድ ላይ የተመሰረተ መሆኑ በሱዳን የተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጉዳቱ ጎረቤት አገራትንም ማወክ ጀምሯል።
የሱዳን የቤጃ ጎሳዎች ተገቢው የፖለቲካ ውክልና አልተሰጠንም በሚል የቀይ ባህር ወደብን ከአንድ ወር በላይ የዘጉ ሲሆን፤ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱን ተከትሎ የአካባቢው መሪዎች በእስር ላይ መሆናቸውን ዘገባው አክሏል።
ባሳለፍነው ሰኞ እለት በሱዳን ጦር አዛዥ ጀነራል አልቡረሃን መሪነት በሲቪል አስተዳድሩ ላይ መፈንቅለ መንግስት ተፈጽሞ የአገሪቱን ሙሉ ስልጣን ወታደራዊ አመራሩ መቆጣጠሩ ይታወሳል።
ጀነራል አልቡርሀን በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይካሄድ ሰግተው መፈንቅለ መንግስት እንደፈጸሙ ቢናገሩም ዓለም አቀፉ ወግዘት ገጥሟቸዋል።
አሜሪካ፤የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች በርካታ የአለማችን አገራት ወታደራዊ አመራሩ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳድሩ እንዲመልስ በማስጠንቀቅ ላይ ሲሆኑ የዓለም ባንክን ጨምሮ አሜሪካ እና ሌሎች አበዳሪ አገራት እና ተቋማት ደጋፋቸውን እንዳቆሙ ተናግረዋል።