የዓለም የምግብ ፕሮግራም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ለደቡብ ሱዳን የሚሰጠው የምግብ እርዳታ አቆመ
ድርጅቱ “በ2022 ስድስት ሚሊዮን የምግብ ዋስትና የሌላቸውን ሰዎች ለመድረስ 426 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል” ብሏል
የእርዳታው ማቆም 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ለረሃብ የተጋለጡ ሰዎች ላሉባት ደቡብ ሱዳን ከባድ አደጋ ነው ተብሏል
የዓለም ምግብ ፕሮግራም (ደብሊው.ኤፍ.ፒ)
በገንዘብ እጥረት ምክንያት ለደቡብ ሱዳን የሚሰጠው የምግብ እርዳታ አቆመ፡፡
የፕሮግራሙ እርዳታ ማቆም 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ለረሃብ የተጋለጡ ሰዎች ላሉባት ደቡብ ሱዳን ከባድ አደጋ የሚፈጥር ነው ተብሏል፡፡
ውሳኔው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን እና በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ አቅመ ደካሞችን የሚጎዳ መሆኑን የገለጸው ደብሊው.ኤፍ.ፒ፤ ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ ካልተበጀለት በስተቀር ሁኔታው አስከፊ መዘዞች ሊመጣ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡
ድርጅቱ “እንደፈረንጆቹ በ2022 ስድስት ሚሊዮን የምግብ ዋስትና የሌላቸውን ሰዎች ለመድረስ 426 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልገኛል” ማለቱም ነው ሲጂቲኤን የዘገበው፡፡
ደብሊው.ኤፍ.ፒ ባወጣው መግለጫ "ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እስካላገኘ ድረስ የበለጠ ከባድ የሬሽን ቅነሳ ማድረጉ አይቀሬ ይሆናል፤ ይህም ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች መሰረታዊ የምግብ ፍላጎታቸውን ማሟላት እንዳይችሉ እና እንደ ምግብ መዝለል ወይም መቀነስ፣ ንብረቶችን መሸጥ፣ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ እና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ወደመሳሰሉ የህልውና አማራጮች እንዲመለሱ ያደርጋል" ብሏል፡፡
ሆኖም ምንም እንኳን ችግሩ ከባድ ቢሆንም ፕሮግራሙ በሃገሪቱ 52 ግዛቶች በከባድ ረሃብ እየተሰቃዩ ያሉትን 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች ለመድረስ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ቀደም ሲልም እንዳስታወቀው በገጠመው የገንዘብ እጥረት ምክንያት በተለያዩ ሀገራት የሚሰጠውን እርዳታ ሙሉ በሙሉ ለማቆም ሊገደድ እንደሚችል ሲያሳስብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ መልኩ ሞዛምቢክ፣ ሶማሊያ እና ማዳጋስካርን ጨምሮ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ህዝቦችን ለመደገፍ ለጋሽ ድርጀቶች እና አጋሮችን በሚልዮን ዶላሮች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቆ እንደነበር አይዘነጋም፡፡