የፀጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ላይ ጥሎት የነበረውን የጦር መሳሪያዎች ማዕቀብ አራዘመ
ምክር ቤቱ በአሜሪካ አቅራቢነት ነው ማዕቀቡን ለተጨማሪ አንድ ዓመት ያራዘመው
ሩሲያን እና ቻይናን ጨምሮ ጋቦን፣ ኬንያ እና ህንድ እንዲራዘም ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ላይ ጥሎት የነበረውን የጦር መሳሪያዎች ማዕቀብ በአንድ ተጨማሪ ዓመት አራዘመ፡፡
ምክር ቤቱ በአሜሪካ አቅራቢነት ነው ማዕቀቡን ለተጨማሪ አንድ ዓመት ያራዘመው፡፡ ከምክር ቤቱ 15 አባላት መካከልም 10ሩ ደግፈውታል፡፡
ሆኖም ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸውን ሩሲያን እና ቻይናን ጨምሮ ጋቦን፣ ኬንያ እና ህንድ ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል፡፡
አሁንም በሃገሪቱ በመካሄድ ላይ ያሉ ግጭቶችንና የመብት ጥሰቶችን በጽኑ ያወገዘው ምክር ቤቱ ከአሁን ቀደም ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ ማራዘሙን ዛሬ አርብ ግንቦት 19 ቀን 2014 ዓ/ም አስታውቋል፡፡
የተራዘመው ማዕቀብ እስከ ቀጣዩ ዓመት ግንቦት ወር የሚዘልቅ ነው፡፡
የምክር ቤቱ አባል የሆኑ የትኞቹም ሃገራት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለጁባ የጦር መሳሪያዎችን እንዳያቀርቡና እንዳይሸጡ ይከለክላል፡፡
ማዕቀቡ ለይቶ ባስቀመጣቸው የሃገሪቱ ባለስልጣናትና ግለሰቦች ላይ የጉዞ እና የሃብት እገዳዎች እንዲደረጉምያዛል፡፡
የጦር መሳሪያ ማዕቀቡ በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት እና በምክትላቸው ሪክ ማቻር (ዶ/ር) ስምምነት ደም አፋሳሽ የነበረው የእርስ በእርስ ግጭት መቆሙን ተከትሎ በፈረንጆቹ 2018 የተጣለ ነው፤ ምንም እንኳን ደቡብ ሱዳን ማዕቀቡ እንዲነሳ ደጋግማ ብትጠይቅም፡፡
ሆኖም ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ደጋግመው ያደረጉትን ተኩስ አቁምና የሰላም ስምምነት የሚጥሱ በመሆኑ ማዕቀቡ ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ መልኩ ለአንድ ዓመት ተራዝሟል፡፡ አሁንም ማዕቀቡ ሊነሳ የሚችለው የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ብቻ መሆኑን ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ ከነጻነት በኋላ በሃገሪቱ የተቀሰቀሰውን የእርስ በእርስ ግጭት ተከትሎ በፈረንጆቹ 2015 ሰፊ ማዕቀብን በደቡብ ሱዳን ላይ መጣሉ ይታወሳል፡፡