የሱዳኑ አብደላ ሀምዶክ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ተመለሱ
ሀምዶክ ወደ ቀድሞ ኃላፊነታቸው የተመለሱት በሱዳን ሀይሎች መካከል የፖለቲካ ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ነው
ሌ/ጄ አብዱልፈታ አልቡርሃንና ጠ/ሚኒስትር አብደላህ ሀምዶክ አዲስ ፖለቲካዊ ስምምነት ተፈራርመዋል
የሱዳኑ አብደላ ሀምዶክ በሀገሪቱ የተፈረመውን አዲስ ፖለቲካዊ ስምምነት ተከትሎ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ተመልሰዋል።
የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን በሀገሪቱ ጦር መፈንቅለ መንግስት ከተፈፀመ ሶስት ሳምንታት በኋላ ስልጣን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ፈርመዋል።
ዛሬ በካርቱም በሚገኘው ቤተ መንግስት ውስጥ የተካሄደውን የፖለቲካ ስምምነትም ሌተናል ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሀምዶክ መፈረማቸው ተነገሯል።
ሌተናል ጀነራል አብዱልፈታህ አል-ቡርሀን እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላህ ሃምዶክ በ14 ጉዳዮችን ዙሪያ መፈራረማቸውም ነው የተገረው።
ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መካከልም ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ እና አንድ ወጥ የሆነ የሱዳን ጦር መመስረት፣ የሱዳንን ግዛታዊ አንድነት ማስጠበቅ፣ የሽግግር ጊዜውን የሚመራውን ሕገ መንግሥታዊ፣ ህጋዊ እና ፖለቲካዊ አስራሮች መወሰን የሚሉት ይገኙበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሀምዶክ ከስምምነቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ አንድነት ለሱዳን አስፈላጊ መሆኑን በማንሳት፤ የሱዳን ጥቅም ማስጠበቅ ቀዳሚ ጉዳይ እንደሆነም አሳስቧል።
“ዛሬ የተፈረመው ስምምነት ለሳምንታት የተሰራ የጠንካራ ስራ ውጤት ነው” ያሉት ሀምዶክ፤ “ሱዳን ምንም መመለስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ብትደርስም መመለስ እንደምትችል ያረጋገጠ ነው” ብለዋል።
ሌተናል ጀነራል አብዱልፈታህ አል-ቡርሀን በበኩላቸው “ዛሬ የተፈረመው ስምምነት የሱዳናውያን የስራ ውጤት ነው፤ ይህ የእውነተኛ ሽግግር ጅማሮ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ብዙዎች “መፈንቅለ መንግስት ነው” ባሉት እርምጃ የሱዳን ጦር ባሳለፍነው ወር የሀገሪቱን የሽግግር መንግስት የሚመሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን ጨምሮ ሲቪል ባለስልጣናትንና ከፍተኛ አመራሮችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወሳል።
በሱዳን በሃገሪቱ ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሃን የሚመራ አዲስ ወታደራዊ መንግስት መመስረቱ የሚታወስ ነው።
ይህንን ተከትሎም በወታደሩ ተግባር የተበሳጩ ሱዳናውያን በካርቱም እና በሌሎችም የሀገሪቱ ጎዳናዎች ላይ በመውጣት ቁጣቸውን ሲገልጹ ነበረ ሲሆን፤ በተቃውሞ ሰልፎቹ ላይ በሱዳን ጦር የተገደሉ ሰላማዊ ሰልፈኞች ቁጥር 40 ደርሷል።
ተመድን ጨምሮም በርካታ ሀገራት ወታደራዊ አመራሩ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳድር እንዲመልስ ድርድር እንዲጀመር ሲወተውቱ መቆየታቸውም አይዘነጋም።