ስልጣኑ ወደ ሲቪል አስተዳድሩ እንዲመለስ ኢጋድ አሳስቧል
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በሱዳን የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት አወገዘ።
በሱዳን በሲቪል አስተዳድሩ ላይ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱ ይታወሳል።
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ኢጋድ በሱዳን በተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ዙሪያ ባወጣው መግለጫ መፈንቅለ መንግስቱ የሱዳናዊያንን ዲሞክራሲ ዝቅ ያደርጋል ብሏል።
በመሆኑም የሱዳን ጦር ያካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ያወገዘው ኢጋድ፤ ስልጣኑ ወደ ሲቪል አስተዳድሩ እንዲመለስም አሳስቧል፡፡
የሱዳንን ጉዳይ በቅርብ እየተከታተለ መሆኑን ያሳወቀው ኢጋድ ለሱዳናዊያን ሲቪል አስተዳድር ድጋፉን እንደሚያደርግም አስታውቋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ በሱዳን አሁን ላይ የተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ በእጅጉ እንዳሳሰበው አስታውቋል።
የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሀመት፥ በሱዳን ያለው አሁናዊ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳየው የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀማዶክ እና ሌሎች የአገሪቱ ሲቪል ባለስልጣናት መታሰራቸው ነው ሲሉ ጉዳዩ ከምንም በላይ እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል።
ሊቀመንበሩ ሙሳ ፋቂ ማሀመት፥ በሲቪሉ አስተዳደር እና በወታደሩ መካከል ያሉ ጉዳዮች በፖለቲካ ውይይትና እና ህገ መንግስታዊ ማዕቀፍ በፍጥነት እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል።
ሀገሪቷን ለመታደግ እና ለዲሞክራሲያዊ ሽግግር ውይይትና መግባባት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነም አስምረውበታል።
ሊቀመንበሩ አክለውም የፖለቲካ መሪዎች ከእስር እንዲፈቱ እና ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ እንዲደረግ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በሱዳን በዛሬው እለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወቃል።
የሱዳን ጦር አዛዥ ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን በመፈንቅለ መንግስቱ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ የሉአላዊ ምክር ቤት እና ሚኒስትሮች ምክር ቤት የፈረሰ ሲሆን የክልሎች አሰተዳዳሪዎች እና ሌሎች አመራሮች ከስልጣን ተነስተዋል።
የሱዳን ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሬም አልሳዴቅ በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ መታሰር አደገኛ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ መሬም ገለጻ ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዳላወሯቸው ገልጸው፤ ከቃል አቀባያቸው ጋር ስለ ጉዳዩ ማውራታቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወዳልታወቀ ስፍራ መወሰዳቸውን ሰምቻለሁ ያሉት መሬም አልሳዴቅ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሱዳናዊያን አብዮት ወኪል መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በመሆኑም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሚደረጉ እንግልቶች እና ጉዳቶች በሱዳናዊያን ላይ ብዙ ጉዳቶችን ያደርሳል ብለዋል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ።
በሱዳን በተካሄደው መፈንቅለ መንግስት አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ አገራት እና ተቋማት ድርጊቱን የኮነኑ ሲሆን የአውሮፓ ህብረት የሱዳን ጦር ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳድር እንዲያስረክብ በማሳሰብ ላይ ናቸው።