የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሀምዶክ ከቁም እስር ተለቀቁ
በሱዳን እየተካሄደ ባለው ድርድር አብደላህ ሀምዶክን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመመለስ ከስምምነት ተደርሷል
ሀምዶክ ከሳምንታት በፊት በሱዳን ጦር ከስልጣናቸው ከተነሱ በኋላ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የቁም እስር ላይ ነበሩ
በቁም እስር ላይ የነበሩት አብደላህ ሀምዶክ መለቀቃቻን የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሀምዶክ ከሶስት ሳምንታት በፊት በሱዳን ጦር ከስልጣናቸው ከተነሱ በኋላ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የቁም እስር ላይ እንደነበሩ ይታወሳል።
“የሱዳን ጦር በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሀምዶክ ላይ ጥሎት የነበረውን እንቅስቀሴ ገደብ አንስቷል” ሲል የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከሰዓታት በፊት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
አብደላህ ሀምዶክ ከእስር የተለቀቁት የሱዳን የፖለቲካ ሀይሎች በትናትናው እለት አዲስ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ እንደሆነም ተነግሯል።
ስምምነቱን ተከትሎም የፖለቲካ ሀይሎቹ በዛሬው እለት ይፋ የሚያደርጉት አዲስ ነገር መኖሩም እየተነገረ ነው ያለው።
ከስምምነቱ ውስጥም አብደላህ ሀምዶክን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መመለስን ጨምሮ አሁን ላለው የሱዳን የፖለቲካ ለውጥ አዲስ ፍኖተ ካርታን ይፋ ማድረግ ይገኝበታል ነው የተባለው።
የሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ሀገሪቱን ከቀውስ ለማውጣት እያካሄዱት ባለው ድርድር ላይ በወታደራዊ ኃይሎች ከስልጣናቸው ተነስተው የነበሩትን አብደላ ሀምዶክ ወደ ቀድሞ ኃላፊነታቸው ለመመለስ ከስምምነት ደርሰዋል።
በተጨማሪም ተደራዳሪ ኃይሎቹ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲለቀቁ፣ የሱዳንን ግዛታዊ አንድነት ማስጠበቅ፣ የሽግግር ጊዜውን የሚመራውን ሕገ መንግሥታዊ ፣ህጋዊ እና ፖለቲካዊ አስራሮች ላይ ለመወሰን ተስማምተዋል።
የሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ሀገሪቱን ከቀውስ ለማውጣት ባካሄዱት ድርድር እና በደረሱባቸው ስምምነቶች ዙሪያ ዛሬ በይፋ እንደሚፈራረሙም ተነግሯል።
ብዙዎች “መፈንቅለ መንግስት ነው” ባሉት እርምጃ የሱዳን ጦር ባሳለፍነው ወር የሀገሪቱን የሽግግር መንግስት የሚመሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን ጨምሮ ሲቪል ባለስልጣናትንና ከፍተኛ አመራሮችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወሳል።
በሱዳን በሃገሪቱ ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሃን የሚመራ አዲስ ወታደራዊ መንግስት መመስረቱ የሚታወስ ነው።
ይህንን ተከትሎም በወታደሩ ተግባር የተበሳጩ ሱዳናውያን በካርቱም እና በሌሎችም የሀገሪቱ ጎዳናዎች ላይ በመውጣት ቁጣቸውን ሲገልጹ ነበረ ሲሆን፤ በተቃውሞ ሰልፎቹ ላይ በሱዳን ጦር የተገደሉ ሰላማዊ ሰልፈኞች ቁጥር 40 ደርሷል።
ተመድን ጨምሮም በርካታ ሀገራት ወታደራዊ አመራሩ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳድር እንዲመልስ ድርድር እንዲጀመር ሲወተውቱ መቆየታቸውም አይዘነጋም።