በሱዳን ጦር የተገደሉ ሰላማዊ ሰልፈኞች ቁጥር 40 ደረሰ
በሱዳን በሃገሪቱ ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሃን የሚመራ አዲስ ወታደራዊ መንግስት መመስረቱ የሚታወስ ነው
የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉ ከካርቱም አልፎ ወደ ሌሎች አጎራባች ከተሞች እየሰፋ ይገኛል ተብሏል
በሱዳን ጦር የተገደሉ ሰላማዊ ሰልፈኞች ቁጥር 40 ደረሰ፡፡
በጀነራል አል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ከአንድ ወር በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በሚመራው ሲቪል አስተዳድር ላይ መፈንቅለ መንግስት በመፈጸም አመራሩንም ማሰሩ ይታወሳል።
መፈንቅለ መንግስቱን ተከትሎ ወታደራዊ አመራሩ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደሩ እንዲመልስ የተለያዩ ጫናዎች በመደረግ ላይ ቢሆንም የሱዳን ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሃን አዲስ ወታደራዊ መንግስት መስርተዋል፡፡
ይሄንን ተከትሎ ሱዳናዊያን አዲሱን የሱዳን ወታደራዊ መንግስት ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ ላይ ናቸው።
የሱዳን ጦርም ሰላማዊ ሰልፎቹን ለመበተን የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ሲሆን አስለቃሽ ጭስን እና ሌሎች መሳሪያዎችን በመጠቀም ላይ መሆኑን ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
ጦሩ እስካሁን በተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በወሰዳቸው እርምጃዎች በትንሹ 40 ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ደግሞ መቁሰላቸውን የሱዳን ሀኪሞች ማህበር ገልጿል፡፡
ሱዳናዊያን ወታደራዊ አመራሩ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳድሩ እስከሚመልስ ድረስ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን እንደማያቆሙ የሱዳን የሙያተኞች ማህበር አስታውቋል፡፡
የተቃውሞ ሰልፉ አሁን ላይ ከአገሪቱ መዲና ካርቱም ወደ ጎረቤት ከተሞች ባህሪ እና ኦምዱርማን ከተሞች እየሰፋ ሲሆን በቀጣይም ወደ ሌሎች ከተሞች እንደሚሰፋ ማህበሩ አክሏል፡፡
በያዝነው ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ በቀጣዮቹ ቀናት ደግሞ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉ በከሰላ፣ ድንጉላ፣ ወደመደኒ እና ጅኔና ከተሞች የሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አስቀድሞ ጥሪ መተላለፉን ዘገባው አክሏል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ሆኖ የሱዳን ጦር በነዚህ ከተሞች ዋና ዋና መተላለፊያ መንገዶች እና አደባባዮች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጦር አስቀድሞ መሰማራቱን ዘገባው አክሏል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት በበኩሉ የሱዳን ጦር በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ጥይት እንዳይተኩስ እና ዜጎችን እንደይጎዳ ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው መግለጫ አስቀድሞ አሳስቧል።