ግብጽ ከአይኤምኤፍ ያገኘችውን ብድር ለኑሮ ውድነት ማረጋጊያ እንደምታውለው ገልጻለች
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ለግብጽ የ3 ቢሊዮን ዶላር ብድር ማጽደቁን ገልጿል።
ተቋሙ ለግብጽ በብድር መልክ ከሚሰጠው ሶስት ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 347 ሚሊዮን ዶላሩን በአስቸኳይ ለግብጽ እንደሚሰጥ ተገልጿል።
ግብጽ ሶስት ቢሊዮን ዶላሩ በ46 ወራት ውስጥ ከተቋሙ እንደሚለቀቅላት ሮይተርስ ዘግቧል።
ግብጽ ከአይኤምኤፍ የምታገኘውን ሶስት ቢሊዮን ዶላር ለኑሮ ውድነት ማረጋጊያ፣ ለማህበራዊ እና ለከተማ የምግብ ዋስትና ስራዎች እንደምታውለው ገልጻለች።
አይኤምኤፍ ግብጽን ጨምሮ ለመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የ14 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚችል አስታውቋል።
የግብጽ የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ በጀት ከሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መጀመር በፊት ከነበረበት 41 ቢሊዮን ዶላር አሁን ላይ ወደ 33 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ማለቱ ተጠቅሷል።
የዓለም ባንክ ከሰሞኑ ለኢትዮጵያ 745 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማጽደቁን የገለጸ ሲሆን ገንዘቡ ለምግብ ዋስትና፣ በጦርነት ለተጎዱ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጥገና እና ሌሎች ስራዎችን ለመከወን ይውላል ተብሏል።
ከሶስት ቀናት በፊት በዋሸንግተን በተካሄደው የአፍሪካ-አሜሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከዓለም ባንክ እና ሌሎች ሀገራት እና ተቋማት መሪዎች ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።
የጠቅላይ ሚንስትሩን ውይይት ተከትሎ ከዓለም ባንክ እና ሌሎች የበለጸጉ ሀገራት ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፎች ለኢትዮጵያ ሊሰጡ እንደሚችሉ ይጠበቃል።