የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለሶማሊያ የሚያደርገውን የገንዘን ድጋፍ ፓኬጅ አራዘመ
የድጋፉ መራዘም ሞቃዲሾ የግሉ ሴክተሯን እንድታዳብር የሚያስችል ነው ተብሏል
የሶማሊያ ዓለም አቀፍ አጋሮች የፕሬዝዳንት ሞሃሙድን መመረጥ በደስታ ተቀብለውታል
ሶማሊያ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ማካሄደዷን ተከትሎ ፤ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ለሶማሊያ የሚያደረገውን የእርዳታ ፓኬጅ እንዳራዘመ አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናግረዋል።
ሶስት አመታት የሚፈጀው የ400 ሚሊዮን ዶላር የአይኤምኤፍ የዕርዳታ ፓኬጅ፤ በግንቦት 17 አዲስ አስተዳደር ባይፈጠር ኖሮ የሚቋረጥ እንደነበር፤ የሶማሊያ የአይኤምኤፍ ተልዕኮ ኃላፊ ላውራ ጃራሚሎ መናገራቸው ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
ነገር ግን የሶማሊያ መንግስት እርዳታው እስከ ነሃሴ 17 ድረስ ለሶስት ወራት እንዲራዘም ለአይኤምኤፍ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት፤ የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ቦርድ መቀበሉ ከፍተኛ ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡
ላውራ ጃራሚሎ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት "ማራዘሙ በአዲሱ መንግስት እና የልማት አጋሮቹ መካከል በፖሊሲዎችና የፋይናንስ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር አስፈላጊውን ጊዜ የሚሰጥ ነው" ብለዋል።
የሶማሊያ ዓለም አቀፍ አጋሮች የአዲሱን ፕሬዝዳንት መመረጥ በደስታ የተቀበሉት ሲሆን፤ ይህም ወደ ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ እንዳታመራ ተፈርቶላት የነበረችውን ሀገር ወደ እድገት ጎዳና እንድትራመድ ያስችላታል ተብሏል፡፡
በአይኤምኤፍ ፕሮግራም ውል መሰረት የሶማሊያ ዕዳ እስከ 2023 ድረስ ወደ 557 ሚሊዮን ዶላር ሊወርድ ይችላል ሲሉ ጃራሚሎ በየካቲት ወር በሰጠው ቃለ ምልልስ ለኤኤፍፒ ተናግረው ነበር።
የጊዜው መራዘም፤ ሞቃዲሾ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንድታገኝ እና የግሉ ሴክተሯን እንድታዳብር ያስችላታልም ብለዋል፡፡
ከዓለማችን ድሃ ሀገራት አንዷ የሆነችው ሶማሊያ፣ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝቧ በቀን ከ1 ነጥብ 90 ዶላር ባነሰ ገቢ የሚኖርባት ሲሆን ፤ ለአስርት አመታት ከዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ለማገገም እየታገለች ትገኛለች፡፡
የቀጠናው ስጋት የሆነው አሸባሪው አልሻባብ እና ድርቅ አሁንም የሀገሪቱ ከፍተኛ ፈተናዎች ሆነው እንደቀጠሉ ነው፡፡
ከቀናት በፊት በምርጫ የሀገሪቱን በትረ ስልጣን የጨበጡት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ “ሰላም የሰፈነባት እና ከዓለም ጋር ሰላም ያላት ሀገር ለማድረግ እሰራለሁ” ማለታቸው የሚታወስ ነው።