በሀገሪቱ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ድምፅ የሚሰጡት የፓርላማ አባላቱ ናቸው
ለወራት የምክር ቤት ምርጫዎችን ለማድረግ ተቸግራ የነበረችው የሶማሊያ አዲስ ፓርላማ ቃለ መሃላ ፈጸመ።
በተለያዩ የምርጫ ክልሎች ተወዳድረው ያሸነፉ 300 ገደማ የላይኛውና የታችኛው ምክር ቤት አባላት ናቸው ቃለ መሃላውን የፈጸሙት።
ሁለቱም የሶማሊያ ምክር ቤቶች በጥቅሉ 329 መቀመጫዎች አሏቸው። ከነዚህ ውስጥ 54 ያህሉ ለላይኛው ምክር ቤት የተመረጡ ናቸው።
ሆኖም ምርጫው አሁንም አልተጠናቀቀም። ያልተሟሉና በድጋሚ ምርጫ የሚካሄድባቸው 16 መቀመጫዎች አሉ።
መቀመጫዎቹ ገርበሃሬ ተብሎ በሚጠራው የሃገሪቱ አካባቢ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች አለመኖሩን ተከትሎ ያልተሟሉ ናቸው።
ሆኖም አሁን የአካባቢው ተወካዮች ጌዶ ተብሎ በሚጠራው ክልል ኢልዋቅ ከተማ በሚሰጥ ድምጽ ሊመረጡ እንደሚችሉ እየተነገረ ይገኛል።
ሶማሊያ ምርጫውን ከጸጥታና ከተለያዩ የልዩነት ምክንያቶች በመነሳት ስታራዝም ነበረ። ይህም በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር ትልቅ ብጥብጥን እንዳይቀሰቅስ ተሰግቶ ነበር።
ህግ አውጪ የምክር ቤቱ አባላት ሲሟሉ ቀጣዩን የሃገሪቱን ፕሬዝዳንት የሚመርጡ ይሆናል።