ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን 220 ሚሊየን የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባቶችን ለአፍሪካ ሀገራት ለማቅረብ ተስማማ
ኩባንያው ክትባቶቹን ለ55 የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት እስከ አውሮፓውያኑ 2021 3ኛ ሩብ ዓመት ድረስ ያቀርባል
ቫይረሱን ከአፍካ ለማስወገድ ቢያንስ 60 በመቶ ህዝብ የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት መውሰድ አለበት- አፍሪካ ሲዲሲ
ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የመድሃት አምራች 220 ሚሊየን የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባቶቹን ለአፍሪካ ሀገራት ለማቅረብ ተስማማ።
ኩባንያው ክትባቶቹን ለ55 የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት እስከ አውሮፓውያኑ 2021 3ኛ ሩብ ዓመት ድረስ የሚቀርብ መሆኑም ታውቋል።
ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የክትባት አቅርቦት ስምምነቱን ከአፍሪካ የኮቪድ 19 ክትባት አፈላላጊ ባለአደራ (አቫት) ጋር የተፈራረመ መሆኑንም ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
ስምምነቱ ውስጥ ተጨማሪ የ180 ሚሊየን ክትባት አቅርቦት የሚገኝበት ሲሆን፤ ይህም ኩባንያው እስከ አውሮፓውያኑ 2022 ድረስ በጃፓን በሚገኘው የመድሃኒት ማመረቻው በኩል ለአፍሪካ ሀገራት የሚደርሰውን የክትባት መጠን 400 ሚሊየን ያደርሰዋል ተብሏል።
የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ጆን ንከንጋሶንግ “ቫይረሱን ከአህጉራችን ለማስወገድ ቢያንስ 60 በመቶው የህዝባችን የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት መውሰድ አለበት” ብለዋል።
ከጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የመድሃኒት አምራች ኩባንያ ጋር የተደረሰው ስምምነትም ይህንን ግብ ለማሳካት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
በያዝነው ወር መጀመሪያ አካባቢ የአውሮፓ ህብረት ለጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት እውቅና የሰጠ ሲሆን፤ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ባህሬንም ክትባቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ቀደም ብለው እውቅና የሰጡ ሀገራት ናቸው።
የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የመድሃኒት አምራች ኩባንያ የሚያመርተው መድሃት በአንድ ዙር ብቻ የሚሰጥ መሆኑም ታውቋል።