የዓለም የገንዘብ ድርጅት የ2023 የዓለም የምጣኔ-ሀብት ምልከታውን አሻሻለ
የዓለም ምጣኔ-ሀብት በዚህ ዓመት በ2 ነጥብ 9 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል
ለአይኤምኤፍ አዲስ ምልከታ ቻይና ምክንያት መሆኗ ታውቋል
የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የዓለም ምጣኔ-ሀብት አስቀድሞ ከነበረው ምልከታ ብሩህ እየሆነ ነው ብሏል።
ቻይና የኮቪድ ፖሊሲዎቿን ማላላቷ እና ዓለም ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ ከፍተኛ የወለድ ተመኖች እና የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ጠባሳን የመቋቋም አቅሟን እያሳየች ባለችበት ወቅት የምጣኔ-ሀብት ምልከታው "በትንሹም ቢሆን" ብሩህ እየሆነ ነው ተብሏል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የዓለም ምጣኔ-ሀብት በአዲሱ ዓመት በ2 ነጥብ 9 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል ብሏል በምልከታው።
ትንበያው በፈረንጆቹ 2022 ከነበረው የ3 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ቢቀንስም አይኤምኤፍ በዓመቱ መባቻ ከተገመተው የ2.7 በመቶ እድገት የተሻለ ነው ተብሏል።
190 አባል ሀገራት ያሉት አበዳሪ ድርጅቱ አይኤምኤፍ በዚህ የፈረንጆቹ ዓመት የዋጋ ንረት እየቀነሰ እንደሚሄድ በትንበያው አስቀምጧል።
በመሆኑም በመጠባበቂያ ክምችት እና በማዕከላዊ ባንኮች ከፍተኛ የወለድ መጠን ይጨምራል። ይህም የዋጋ ጭማሪ ያስከተለውን የሸማቾች ፍላጎት ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል ማለቱይ ታይምስ መጽሔት ዘግቧል።
ድርጅቱ የዓለም አቀፍ እድገት ማሻሻያ ትልቅ ምክንያት የሆነችው ቻይና የኮቪድ እርምጃዎችን ማላላቷ ከሚጠበቀው በላይ ምጣኔ-ሀብት እንዲያገግም መንገዱን ይከፍታል ብሏል።