የአሜሪካ የውጭ ዕርዳታ መቆሙ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምን ይመስላል?
በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከስራ ገበታቸው እንደሚፈናቀሉ ዩ.ኤን-ኤድስ ኢትዮጵያ አስታውቋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/07/252-180856-whatsapp-image-2025-02-07-at-5.06.20-pm_700x400.jpeg)
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኤች አይቪ ኤድስ ህሙማን የድጋፍ አገልግሎት አደጋ ላይ ይወድቃል
የአሜሪካ የውጭ ዕርዳታ በመቆሙ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል ፕሮግራም (ዩ.ኤን-ኤድስ ኢትዮጵያ) አስታወቀ።
ከአንድ ወር በፊት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ወደ ስልጣን የመጡት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ የረድኤት ድርጅት ወይም ዩኤስኤይድ ከአስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታዎች ውጪ ሌሎች ስራዎቹን እንዳይሰራ ማገዳቸው ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም ከድርጅቱ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ሀገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡
ዩ.ኤን-ኤድስ ኢትዮጵያ በደረ ገጹ ባወጣው መረጃ ዩናይትድ ስቴትስ ለማህበረሰብ ፕሮግራሞች የምትሰጠው እርዳታ በማቆሟ ለኤችአይቪ መከላከል እና የሳንባ ነቀርሳ ምርመራዎች፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖችን እና ሥርዓተ-ፆታን መሰረት ያደረገ ድጋፍን የመሳሰሉ ወሳኝ አገልግሎቶችን አቋርጧል ብሏል።
የገንዘብ ድጋፉ አስፈላጊ የሆኑትን የኤችአይቪ ኤድስ የመመርመሪያ ኪት እና ሌሎች ግብአቶችን ጨምሮ አገልግሎቶች አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መዘግየት እና እጥረት አስከትሏል ብሏል።
በተጨማሪም በተለያዩ ዘርፎች የሚሰሩ ሰራኞች ከስራ ውጪ ማድረጉንም የተመድ የኤች አይ ቪ ኤድስ ፕሮግራም (ዩ.ኤን-ኤድስ ኢትዮጵያ) አስታውቋል።
የአሜሪካ የውጭ ዕርዳታ መቆሙን ተከትሎ የመረጃ ማሰባሰብ ስራ ላይ የተሰማሩ 10 ሺህ የመረጃ ምዝገባ ሰራተኞች የስራ ውል መቋረጡን ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።
የስራ ውላቸው የተቋረጠው ሰራኞች በጤና አጠባበቅ ማጅመንት ሲስተም ቋት ላይ መረጃ የሚያስገቡ እንደነበሩም ነው የተገለጸው።
የጤና ሚኒስቴር በመላው ሀገሪቱ በአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ ተቀጥረው ሲሰሩ የነበሩ የ5 ሺህ የህብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች ኮንትራት መቋረጡን እንዳስታወቀም ነው ዩ.ኤን-ኤድስ ኢትዮጵያ ያመላከተው።