ከመተከል የተፈናቀሉ አማራዎችን በ1 ወር ውስጥ መልሶ ለማቋቋም ይሰራል ተባለ
በአካባቢው ግጭት እንዲፈጠርና ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉ ያደረጉ አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱ ይቀጥላልም ተብሏል
ከመተከል ዞን የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች በአንድ ወር ውስጥ ወደ ቀያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ይሰራል ተባለ
ከአሁን ቀደም በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ሳቢያ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆችን በቀጣዩ አንድ ወር ውስጥ ወደ ቀያቸው መልሶ ለማቋቋም እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡
ሁኔታውን አስመልክተው በባህርዳር የመከሩት የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆኑ አመራሮች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል እንደ አማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ዘገባ፡፡
ችግሩን ፈትተን ተፈናቃዮችን በቶሎ ወደ ቀያቸው ለመመለስና አርሶአደሩን ወደ እርሻው ለማሰማራት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን ተወያይተናል ያሉት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በቀጣይ አንድ ወር ውስጥ የሁለቱም ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ተሰማርተው መተከልን የጋራ ማዕከል አድርጎ የተፈናቀሉ ሰዎችን ቶሎ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እንዲሰሩ ለማድረግ የሚያስችል ውይይትን አድርገናል ብለዋል፡፡
በአካባቢው የሚታዩ ዝርፊያዎችን እና ህገወጥ ተግባራትን ተከታትሎ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን ለመስራት አቅጣጫ አስቀምጠናል ያሉም ሲሆን የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸውና ህዝቦችን የሚያጋጩ እንዲፈናቀሉ ከሚያደርጉ አካላት ጋር በተያያዘ የለየናቸው ጉዳዮችም አሉ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
”እነዚህ ጉዳዮች ጥብቅ እርምጃን ይፈልጋሉ ስለዚህ እንደ እኛ ክልል የጀመርናቸው የህግ የበላይነትን የማስከበር እርምጃዎች አሉ ህዝቡ የተፈናቀሉትን መልሱልን እጃቸውን የሚያስገቡ አመራሮችን ቡድኖችን የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸውንም አካላት አስታግሱልን ሲል እየነገረን ስለሆነ አእነሱን አጠናክረን እንቀጥላለን“ በሚልም ነው ያስቀመጡት፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው በቀጣይ አንድ ወር ተፈናቃዮቹን የመመለስ ብቻም ሳይሆን የተመለሰውን የመጠበቅ ወደ ምርት ስራ እንዲገባ የማድረግ ስራ እንሰራለን ብለዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ የሚመለስባቸውን ቤቶች የመገንባት የተጀመረውንም ጥረት የማጠናቀቅ ስራም እንሰራለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የራሳቸውን ደህንነት ማስጠበቅ እስከሚችሉ ድረስ ድጋፍ ማድረግ አለብን በሚል መነጋገራቸውንም ገልጸዋል፡፡
አቶ ተመስገን በአንድ ፓርቲ ስር ሆነው በህብረተሰቡ መካከል ችግሮች እንዲፈጠሩ የሚያደርጉ ካሉ በመወያየት እርምጃ እንዲወሰድ እናደርጋለን ያሉም ሲሆን ህብረተሰቡ የራሱንና የአካባቢው ጸጥታ እንዲጠብቅ የሌሎችን ባህልና ወግ አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቂቀጥሉ ለማድረግ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
እንደ አ.ብ.መ.ድ ዘገባ ከሆነ በግጭቱ ምክንያት ከ15ሺ በላይ አማራዎች ከአካባቢው ተፈናቅለዋል፡፡