በምርጫ ጣቢያዎች ከተገኙት ተመዝጋቢዎች 23 በመቶ ያህሉ የፊትና ፊት መከለያ ጭምብል (ማስክ) አለማደረጋቸው ተነግሯል
የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህብረት ለምርጫ የተሰኘው ተቋም "ምርጫ እና ኮሮና ቫይረስ" በሚል በአገር አቀፍ ደረጃ ያካሄደውን ጥናት ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ተቋሙ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች 144 ታዛቢዎቹን በ1 ሺህ 190 ምርጫ ጣቢያዎች ማሰማራቱን ገልጿል።
የህብረቱ አስተባባሪ አቶ ቢንያም አባተ እንደገለጹት በምርጫ ጣቢያዎች ያለው የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶች አተገባበር ሁኔታን ታዛቢዎቹ ባደረጉት ምልከታ 48 በመቶ ያህሉ ብቻ የአፍ እና አፍንጫ መከለያ አድርገዋል።
13 በመቶ ያህሉ የምርጫ አስፈጻሚዎች ብቻ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ አላደረጉም ብሏል ህብረቱ።
በህብረቱ ምልከታ ከተደረገባቸው ምርጫ ጣቢያዎች 23 በመቶዎች ምርጫ ተመዝጋቢዎች ሙሉ ለሙሉ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ወይም ማስክ እንዳላደረጉ ተገልጿል።
ምርጫ ቦርድ በኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በሚል ባዘጋጀው የምርጫ መመሪያ ላይ ሁሉም የምርጫ አስፈጻሚዎች ምስል እና የእጅ ጓንት እንዲያደርጉ በግዴታነት ቢጥልም 60 በመቶ የምርጫ አስፈጻሚዎች ግን የእጅ ጓንት እንዳላደረጉ የህብረቱ ሪፖርት ያሳያል።
እንዲሁም ቦርዱ በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች የኮሮና ቫይረስ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ለማስተማር እና መፈጸማቸውን የሚያረጋግጥ የጤና ባለሙያ እንዲመደቡ ቢደነግግም ምልከታ ከተካሄደባቸው 1ሺህ 190 ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ 89 በመቶ ያህሉ የህክምና ባለሙያ አልተመደበባቸውም ተብሏል።
ማህበሩ በቀጣዩ ምርጫ ላይ 4 ሺህ የምርጫ ታዛቢዎችን እንደሚያሰማራም አስታውቋል።
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ኢማን አብዱልሀኪም በበኩላቸው ቦርዱ በምርጫ ጣቢያዎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል ።
በምርጫ ጣቢያዎች የሳኒታይዘር እና ሌሎች መከላከያ ቁሳቁሶች እጥረት አጋጥሟል የድምጽ መስጫ ቀን ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት ዝግጅቱ ተጠናቋል ብለዋል።
በምርጫ ጣቢያዎች የህክምና ባለሙያ እንዲመደብ የግድ ቢሆንም የተመደቡት ባለሙያዎቹ ተጨማሪ ስራዎች ስላሉባቸው የተባለው ችግር አጋጥሟል ሲሉም ዶ/ር ኢማን ተናግረዋል።
ማህበሩ ያቀረበውን የምልከታ ሪፖርት ይዘን በቀጣይ በሚከናወኑ የምርጫ ስራዎች ላይ እናስተካክላለንም ነው ዶ/ር ኢማን ያሉት።