ሩሲያ እስካሁን 2,631 ዜጎቿ በቫይረሱ መሞታቸውን የገለጸች ሲሆን ምዕራባውያን ቁጥሩን የፖለቲካ ጨዋታ ብለዋል
ሩሲያ እስካሁን 2,631 ዜጎቿ በቫይረሱ መሞታቸውን የገለጸች ሲሆን ምዕራባውያን ቁጥሩን የፖለቲካ ጨዋታ ብለዋል
በአንድ ሳምንት ጊዜ ዉስጥ በርካታ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች የተገኙባት ሩሲያ እስካሁን በድምሩ በቫይረሱ 281,752 ዜጎቿና ነዋሪዎቿ በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጣለች፡፡ በሀገሪቱ ከሚገኙ የቫይረሱ ተጠቂዎች መካከል ደግሞ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በዋና ከተማዋ ሞስኮ የሚኖሩ ናቸው፡፡
ምንም እንኳን በቆዳ ስፋቷ የዓለማችን ቀዳሚ ሀገር በሆነችው በሩሲያ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከፖለቲካ ባላንጣዋ አሜሪካ ጋር ሲነጻጸር እጅግ ዝቅተኛ ቢሆንም እየተጓዘ ያለበት ፍጥነት ግን አሳሳቢ ነው፡፡
ከግዛቷ መለጠጥ ጋር በተያያዘ 11 የሰዓት አቆጣጠር ዞኖች ያሏት ሩሲያ ከማእከል እጅግ የራቁ ጠረፋማ አካባቢዎቿን ጨምሮ በመላ ግዛቷ ቫይረሱ ተዳርሷል፡፡
ከቀናት በፊት ከሀገሪቱ 85 ክልሎች መሪዎች ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ዉይይት ያደረጉት ፕሬሲዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ሁኔታዎችን እየተከታተሉ ቫይረሱን ለመከላከል የተጣሉ እገዳዎችን የማንሳት አሊያም የማቆየት ኃላፊነት የየክልሎቹ መሪዎች መሆኑን ነግረዋቸዋል፡፡ “ሰፊ ሀገር ነው ያለን” ያሉት ፕሬዚዳንቱ የቫይረሱ ሁኔታ ከቦታ ቦታ ስለሚለያይ ሁኔታዎችን በመከታተል እገዳዎችን የማንሳት እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ማስጀመር በተናጥል መከናወን አለበት ብለዋል፡፡
ሩሲያ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ፣ በተለይም ሞትን በተመለከተ፣ ሪፖርት የምታደርገው መረጃ በሀገሪቱ ካለው እውነታ ጋር እንደማይጣጣም አሜሪካና ሌሎች ምእራባውያን እየገለጹ ነው፡፡ 282 ሺ ገደማ የቫይረሱ ተጠቂዎች ያሉባት ሀገር የሟቾቿ ቁጥር 2,631 ብቻ ነው ማለቷ ለተቀናቃኞቿ አልተዋጠላቸውም፡፡ ከሩሲያ ያነሰ ታማሚ ያላቸው፣ ነገር ግን በጤና ሲስተማቸው ከሩሲያ ያንሳሉ ተብለው የማይታመኑ ፣ በተጠቂዎች ቁጥር 8ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘውን ጀርመንን ጨምሮ የአውሮፓ ሀገራት በቫይረሱ የሞቱባቸው ሰዎች ቁጥር ሩሲያ ሪፖርት ካደረገችው እጅግ ይልቃል፡፡
ምእራባውያኑ ሀገሪቱ የሟቾችን ቁጥር የፖለቲካ ጨዋታ አድርጋለች የሚል እምነት አላቸው፡፡ ለሩሲያ የሟቾች ቁጥር ሪፖርት ትክክለኛ አለመሆን ማሳያ ተደርጎ የቀረበው ደግሞ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ክልሎች የራሳቸውን የተናጥል ሪፖርት ማውጣት ከጀመሩ ወዲህ፣ በክልሎች እና በሀገሪቱ መንግስት የሚወጡ የሟቾች ቁጥር መረጃዎች መለያየታቸው ነው ሲኤንኤን እንደዘገበው፡፡ ለአብነትም ካሊኒግራድ ክልል ባለፈው ዓርብ 13 ሰዎች መሞታቸውን ሪፖርት ሲያደርግ የሀገሪቱ የኮሮናቫይረስ ማእከል የክልሉን ሟቾች 11 ብሎ አቅርቧል፡፡ በሌላ ቼሊያብኒስክ የተባለ ክልል ደግሞ ማእከላዊው መንግስት ሪፖርት ካደረገው የሟቾች ቁጥር በተጨማሪ 10 ሞት ሪፖርት አድርጓል ይላል የሲኤንኤን ዘገባ፡፡
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከ አንድ ወር በፊት የቫይረሱን ስርጭት ተቆጣጥረናል እስከማለትም ደርሰው ነበር፡፡
ባጠቃላይ እስካሁን በመላው ዓለም ከ4 ሚሊዮን 745 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከ313 ሺ በላይ የሚሆኑት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በቫይረሱ ከተያዙት አጠቃላይ ሰዎች ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት አሜሪካውያን እና የአሜሪካ ነዋሪዎች ሲሆኑ በሀገሪቱ ከ90 ሺ በላይ ሰዎች ሞተዋል፡፡