ካናዳም አስቀድማ የህንድን ከፍተኛ የደህንነት ሹም ከኦቶዋ አባራለች
ህንድ በኒው ደልሂ የሚገኙትን የካናዳ ዲፕሎማት በአምስት ቀናት ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አሳሰበች።
ኒው ደልሂ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ካናዳ የህንድ ከፍተኛ የደህንነት ሹምን ከኦቶዋ ባባአረች በስአታት ልዩነት ነው።
የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያሻከረው ጉዳይ በሰኔ ወር ከተገደሉት የሲክ ተገንጣይ ቡድን መሪው ሃርዴፕ ሲንግ ኒጃር ግድያ ነው።
ካናዳ በትናንትናው እለት ባወጣችው መግለጫ ኒጃር በህንድ መንግስት ትዕዛዝ ስለመገደላቸው አስተማማኝ መረጃ አለኝ ማለቷ ኒው ደልሂን አስቆጥቷል።
የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የካናዳን መግለጫ “የተድበሰበሰ እና የተቀነባበረ” ነው ብሎታል።
የካናዳ ዲፕሎማቶች በህንድ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃገብነታቸውና በካናዳ በሚደረጉ ጸረ ህንድ የሆኑ ተግባራት የሚያደርጉት ተሳትፎ መጨመሩ እንዳሳሰበውም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው።
ሃርዴፕ ሲንግ ኒጃር ማን ነው? የሲክ የነጻነት እንቅስቃሴስ?
በፑንጃብ ግዛት የሚገኙት የሲክ ህዝቦች ነጻ ሀገር የመመስረት ትግል የጀመሩት በፈረንጆቹ 1980 እንደሆነ የሬውተርስ ዘገባ ያወሳል።
የመገንጠል እንቅስቃሴውን ለመግታትም የህንድ ወታደሮች በ1984 ከ400 በላይ የሲክ ማህበረሰብ አባላት ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን ዘገባው ያወሳል።
በወቅቱ ወታደራዊ እርምጃውን ያዘዙት የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢንድራ ጋንዲም በጥቅምት ወር 1984 ከሲክ ወገን በሆኑ ሁለት ሴት ጠባቂዎቻቸውን መገደላቸው ነው የሚነገረው።
ከኢንድራ ጋንዲ ግድያ በኋላ በነዚህ ነጻ ሀገር ለመመስረት በሚንቀሳቀሱ ህዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት መድረሱን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላም “ካሊስታኒስ” እያሉ በሚጠሯቸው የሲክ ህዝቦች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዳቸውን የመብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።
ኒው ደልሂ ባለፈው አመትም የሲክ ህዝቦችን መገንጠል የሚያቀነቅነውን ቡድን መሪ ሃርዴፕ ሲንግ ኒጃር ለጠቆመኝ ጠቅም ያለ ሽልማት እሰጣለሁ ማለቷ የሚታወስ ነው።
ኒጃር እና የሚመሩት ተገንጣይ ቡድንን እንደ ሽብርተኛ የምትቆጥረው ህንድ እንቅስቃሴው የብሄራዊ ደህንነቴ ስጋት ነው በማለት በህግ አግዳዋለች።
ይሁን እንጂ እንቅስቃሴው በሰሜን ህንድ፣ ካናዳ እና ብሪታንያ ድጋፍ እንዳለው ነው የሚነገረው።
በርካታ የሲክ ዲያስፖራዎች በሚገኙባት ካናዳ ነዋሪ የነበሩት ሃርዴፕ ሲንግ ኒጃር የሲክ ወይንም "ካሊስታን"ህዝብ የራሱን ሀገር እንዲያቋቋም ህዝብ ወሳኔ ለማድረግ ቅስቀሳ ላይ እያሉ በካናዳ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ በሰኔ ወር ተገድለዋል።
ካናዳ በግድያው የህንድ መንግስት ተሳትፎ አለበት ማለቷም የሀገራቱን ግንኙነት አሻክሮታል።