ህንድ ስድስት የካናዳ ዲፕሎማቶች በአምስት ቀናት ውስጥ ከሀገሪቱ እንዲወጡ አዘዘች
ኒው ደልሂ ውሳኔውን ያሳለፈችው ኦታዋ ስድስት የህንድ ዲፕሎማቶችን ማባረሯን ተከትሎ ነው
የሲክ ተገንጣይ ቡድን መሪ ሃርዴፕ ሲንግ ኒጃር ግድያ የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሻክሯል
ህንድ እና ካናዳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ የሚያሻክር ውሳኔ አሳልፈዋል።
የካናዳ መንግስት ስድስት የህንድ ዲፕሎማቶችን ማባረሩን ማሳወቁን ተከትሎ ህንድም ተመሳሳይ የአጻፋ እርምጃ ወስዳለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶው የሀገሪቱ ፖሊስ ያደረገው ምርመራ ከሲክ ተገንጣይ ቡድን መሪ ሃርዴፕ ሲንግ ኒጃር ግድያ ጀርባ የህንድ መንግስት እንዳለበት አረጋግጧል ብለዋል።
የህንድ መንግስት “ወንጀልን የሚደግፍ ከባድ ጥፋት ፈጽሟል” ያሉት ትሩዶው፥ የወንጀል ድርጊቱን ለማስቆምና የካናዳውያንን ደህንነት ለማስጠበቅ ስድስት የህንድ ዲፕሎማቶችን ለማባረር ወስነናል ሲሉ ተደምጠዋል።
ህንድ በበኩሏ ኦታዋ ለምታቀርበው ክስ እስካሁን ምንም አይነት ማስረጃ አላቀረበችም በሚል ውንጀላውን “አስቂኝ” ነው በማለት ተቃውማዋለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶው በካናዳ የሚኖሩ በርካታ የሲክ ማክበረሰብ አባላትን ለፖለቲካቸው እየተጠቀሙባቸው ነው ብሏል።
ጊዜያዊ ከፍተኛ ኮሚሽነሩን ስቴዋርት ሮስ ዊለርን ጨምሮ ስድስት የካናዳ ዲፕሎማቶች በአምስት ቀናት ውስጥ ኒው ደልሂን ለቀው እንዲወጡም አሳስቧል።
የሲክ ተገንጣይ ቡድን መሪ ሃርዴፕ ሲንግ ኒጃር በሰኔ ወር 2023 ከተገደለ በኋላ የህንድ እና ካናዳ ግንኙነት ሻክሯል። ሀገራቱ ዲፕሎማቶችን በማባረር ተቃውሟቸውን ሲገልጹም የትናንቱ የመጀመሪያቸው አይደለም።
ሃርዴፕ ሲንግ ኒጃር ማን ነው? የሲክ የነጻነት እንቅስቃሴስ እንዴት ተጀመረ?
በፑንጃብ ግዛት የሚገኙት የሲክ ህዝቦች ነጻ ሀገር የመመስረት ትግል የጀመሩት በፈረንጆቹ 1980 ነው።
የመገንጠል እንቅስቃሴውን ለመግታትም የህንድ ወታደሮች በ1984 ከ400 በላይ የሲክ ማህበረሰብ አባላት ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን የሬውተርስ ዘገባ ያወሳል።
በወቅቱ ወታደራዊ እርምጃውን ያዘዙት የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢንድራ ጋንዲም በጥቅምት ወር 1984 ከሲክ ወገን በሆኑ ሁለት ሴት ጠባቂዎቻቸው መገደላቸው ነው የሚነገረው።
ከኢንድራ ጋንዲ ግድያ በኋላ በነዚህ ነጻ ሀገር ለመመስረት በሚንቀሳቀሱ ህዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ደርሶባቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላም “ካሊስታኒስ” እያሉ በሚጠሯቸው የሲክ ህዝቦች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዳቸውን የመብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።
ኒው ደልሂ በ2022 የሲክ ህዝቦችን መገንጠል የሚያቀነቅነውን ቡድን መሪ ሃርዴፕ ሲንግ ኒጃር ለጠቆመኝ ጠቅም ያለ ሽልማት እሰጣለሁ ማለቷ የሚታወስ ነው።
ኒጃር እና የሚመሩት ተገንጣይ ቡድንን እንደ ሽብርተኛ የምትቆጥረው ህንድ እንቅስቃሴው የብሄራዊ ደህንነቴ ስጋት ነው በማለት በህግ አግዳዋለች።
ይሁን እንጂ እንቅስቃሴው በሰሜን ህንድ፣ ካናዳ እና ብሪታንያ ድጋፍ እንዳለው ነው የሚነገረው።
በርካታ የሲክ ዲያስፖራዎች በሚገኙባት ካናዳ ነዋሪ የነበሩት ሃርዴፕ ሲንግ ኒጃር የሲክ ወይንም "ካሊስታን" ህዝብ የራሱን ሀገር እንዲመሰርት ህዝብ ወሳኔ ለማድረግ ቅስቀሳ ላይ እያሉ በካናዳ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ በሰኔ ወር 2023 መገደላቸው ይታወሳል።