እስራኤል “አሜሪካን እሰማለሁ ውሳኔዬ ግን በብሄራዊ ጥቅሜ ላይ የተመሰረተ ነው” አለች
ኔታንያሁ ሀገራቸው በኢራን ላይ የምትወስደው የአጻፋ እርምጃ በወታደራዊ ተቋማት ላይ የተገደበ መሆኑን ለባይደን ነግረዋቸዋል ተብሏል
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሊካሄድ ሶስት ሳምንታት ብቻ ቀርተዋል
እስራኤል ከአጋሯ አሜሪካ የሚቀርቡ ምክረሃሳቦችን ብትሰማም ብሄራዊ ጥቅሟ ላይ መሰረት ያደረገ ውሳኔ እንደምታሳልፍ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ጽህፈት ቤቱ መግለጫውን ያወጣው እስራኤል ለኢራን የባለስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ምን አይነት የአጻፋ እርምጃ ትወስዳለች ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው።
ዋሽንግተን ፖስት እንዳስነበበው ቴል አቪቭ በቴህራን የኒዩክሌር እና የነዳጅ ጣቢያዎች ላይ እርምጃ እንዳትወስድ ዋሽንግተን ስትወተውት ቆይታለች።
በነዳጅ ማምረቻ ጣቢያዎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት የነዳጅ ገበያው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚኖረውም ነው ያስታወቀችው።
ፕሬዝዳንት ባይደን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም ከቀናት በፊት ለ30 ደቂቃ የወሰደ የስልክ ውይይት ሲያደርጉም በአጻፋ እርምጃው ዙሪያ መምከራቸውን አስታውሷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ግን “ከአሜሪካ የሚቀርቡ አስተያየቶችን እናደምጣለን፤ ነገር ግን የመጨረሻ ውሳኔያችን የምናሳልፈው ብሄራዊ ጥቅማቸውን መሰረት በማድረግ ነው” ብሏል።
ዋሽንግተን ፖስት ለጉዳዩ ቅርበት አላቸው ያላቸውን ባለስልጣናት ጠቅሶ ይዞት በወጣው ዘገባ ግን ኔታንያሁ ለባይደን አስተዳደር እፎይታ የሚሰጥ መልዕክት መላካቸውን አመላክቷል።
ከኢራን ጋር ወደለየለት ጦርነት ላለመግባት የአጻፋ እርምጃው በቴህራን ወታደራዊ ተቋማት ላይ ብቻ የተወሰነ እንደሚሆን ማረጋገጫ ሰጥተዋል ነው የተባለው።
እስራኤል “ትልቅ ስህተት ሰርታለች” ባለቻት ኢራን ላይ ከባድ የአጻፋ እርምጃ እንደምትወስድ ስትዝት ብትቆይም ምንም አይነት እርምጃ ሳትወስድ ሁለት ሳምንታት ተቆጥረዋል።
እርምጃው የዘገየውና አስቀድሞ ሲነገር የነበረውን የኒዩክሌር ጣቢያዎች የማፈራረስ እቅድ የተሰረዘው ምናልባትም በቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጥላ እንዳያጠላ በማሰብ ሊሆን እንደሚችል ሬውተርስ ዘግቧል።
እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከጀመረች ወዲህ ከ17 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ያደረገችው አሜሪካ ከ42 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈውን ጦርነት ማስቆም አለመቻሏ በባይደን አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ትችት ሲያስነሳ ቆይቷል።
ባይደን እና ኔታንያሁ በጋዛው ጦርነት ምክንያት በተደጋጋሚ ቅራኔ ውስጥ መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን፥ እስራኤል በኢራን ላይ የምትወስደው የአጻፋ እርምጃ የቀጠናውን ውጥረት ይበልጥ እንዳያባብሰው ስጋት ፈጥሯል።
ዋሽንግተን አጋሯን ቴል አቪቭ ለመከላከል ተጨማሪ ወታደሮችና የጦር መርከቦችን ወደመካከለኛው ምስራቅ ብትልክም የቴል አቪቭ የአጻፋ እርምጃ ቀውስ እንዲፈጥር እንደማትፈልግ አስታውቃለች።
በተለይም ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ልታካሂድ የሶስት ሳምንት እድሜ በቀረበት በአሁኑ ወቅት ከእውቅናዋ ውጪ የሚፈጸም እርምጃን “እንደ ምርጫ ጣልቃገብነት ልትቆጥረው ትችላለች” ብሏል ዋሽንግተን ፖስት በዘገባው።
የባህረ ሰላጤው ሀገራትም እስራኤል የአየር ክልላቸውን አልፋ በኢራን የነዳጅና የኒዩክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት እንዳታደርስ አሜሪካ ጫና እንድታደርግ ጥሪ እያቀረቡ ነው።
ቴህራን የባህረ ሰላጤው ሀገራት ለእስራኤል የአየር ክልላቸውን ከከፈቱ ጥቃት እንዳደረሱብኝ ቆጥሬ እርምጃ እወስድባቸዋለሁ ስትል መዛቷ ይታወሳል።