አዲስ በተወለደ ልጃቸው ስም ላይ ያልተስማሙት ባለትዳሮች ወደ ፍርድ ቤት አቅንተዋል
ባልና ሚስት ልጃቸው እንዲጠራ በሚፈልጉበት ስም ለ3 አመታት በዘለቀ ልዩነት ምክንያት ለፍቺ ያደረሰ ጥል ተጣልተዋል
ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ጥንዶቹ የስም ዝርዝሮችን በመስጠት ባለትዳሮቹን አስማምቷል
ፍጹም ተፈጥሯዊ ጸጋ የሆነው ዘርን መተካት ወይም አይን በአይን ማየት በልጅ ውስጥ ራስን ከመመልከት ባለፈ ወላጆች ልጆቻውን በሚቀርጹበት መንገድ ትክክለኛውን አስተዳዳግ ይዘው እንዲያድጉ ይጥራሉ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የሚወለደው ህጻን የሚጠራበት ስያሜ ከሀይማኖት፣ ከሕይወት ልምድ፣ ከባህል እና ከሌሎችም ማህበራዊ ሁኔታዎች ተቀድቶ ይወሰናል፡፡
አንዳንዶች የልጆቻቸውን ስም ፍቅረኛ ከመያዛቸው ትዳር ከመስረታቸው በፊትም አዘጋጅተው የሚጠባበቁ አሉ ሌሎች ደግሞ ቦታው ላይ ሲገኙ ስሙን ተስማምተው ያወጣሉ፡፡
በጥንዶች መካከል በልጅ ስያሜ የሀሳብ ልዩነት መፈጠር አዲስ ነገር አይደለም ከወደ ህንድ የተሰማው የስም ውዝግብ ግን ለውሳኔ ወደ ፍርድት ቤት አቅንቷል፡፡
የደቡባዊ ህንድ ግዛት ካርናታካ ባለትዳሮች የወንድ ልጃቸውን ስም በተመለከተ ለሶስት አመት የቆየውን ውዝግብ ፍርድ ቤት ጣልቃ ገብቶ እንዲዳኛቸው ወስነዋል፡፡
ነገሩ የተጀመረው በ2021 ነው ህንዳዊቷ እናት ወንድ ልጅ በሰላም መገላገሏን ተከትሎ በህንድ ባህል መሰረት ለማገገም እና ዕረፍት ለማድረግ ወደ ወላጆቿ ቤት ታቀናለች፡፡
ቀጥሎም ባል ለልጁ ባወጣለት ስም አለመስማማቷን ስትገልጽ ግጭት ይፈጠራል በዚህ ሂደት አንድ ሁለት እያለ ለሶስት አመታት ያልተፈታው ጭቅጭቅ ባለትዳሮቹን ለአመታት በተለያየ ቤት እንዲኖሩ ምከንያት ሆኗል፡፡
ይህን ተከትሎም ለፍቺ ወደ ፍርድ ቤት ያቀናችው ሚስት ከባሏ ጋር ለመለያየት ያደረሳቸው ምክንያት በልጃቸው ስም አለመስማማት መሆን ፍርድ ቤቱን አስገርሟል፡፡
ጥንዶቹ ላለመስማማት ያበቃቸውን ምክንያት የተከታተለው ፍርድ ቤት በመጨረሻም የስም ዝርዝሮችን በማዘጋጀት ባልትዳሮቹ ሊስማሙበት የሚችል አንድ ስም ማግኝት ችሏል፡፡
ህጻኑ በአሁኑ ወቅት “አርያቫርድሃና” የሚል ስያሜ በፍርድ ቤት የወጣለት ሲሆን ትርጉሙም “መኳንንት” ማለት ነው፡፡
ከፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ ለሶስት አመታት ተነጣጥለው የኖሩት ጥንዶች ትዳራቸውን ለመቀጠል ተስማምተዋል፡፡