በህንድ ሆስፒታል ውስጥ የተነሳ የእሳት ቃጠሎ የ10 ጨቅላ ህጻናትን ህይወት ቀማ
44 ህጻናትን ከአደጋው መታደግ የተቻለ ሲሆን 16ቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ ናቸው ተብሏል
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ “ልብን በሚሰብረው አደጋ ህጻናት ልጆቻቸውን ላጡ ወላጆች መጽናናትን እመኛለሁ" ብለዋል
በሰሜናዊ ህንድ በሚገኝ የመንግስት ሆስፒታል ውስጥ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ 10 አዲስ የተወለዱ ህጻናት ህይወት አለፈ።
አርብ ምሽት በማሃራኒ ላክስሚ ባይ ሜዲካል ኮሌጅ ሆስፒታል የደረሰው የእሳት ቃጠሎ በኤሌክትሪክ ችግር የተከሰተ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የህንድ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት እሳቱ በመጀመሪያ የተቀሰቀሰው በጨቅላ ሕፃናት ክፍል ውስጥ ሲሆን በማቆያ ክፍሉ ውስጥ ያለውን የኦክስጂን መጠን ለመጨመር ጥቅም ላይ የዋለው የኤሌክትሪክ ስርአት ላይ ባጋጠመ ብልሽት ነው አደጋው የተከሰተው።
በኡታር ፕራዴሽ ግዛት በጃንሲ ከተማ የሚገኘው ሆስፒታል ሰራተኞች ክፍሉን ሰብረው ገብተው 44 ጨቅላ ህጻናትን ማዳን ችለዋል። ነገርግን ቢያንስ 16ቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል ።
ከስፍራው የወጡ ምስሎች ከሆስፒታሉ ውጪ በሀዘን ውስጥ የሚገኙ እና የሚያለቅሱ ወላጆችን አሳይተዋል። በተጨማሪም እስካሁን የሶስት ህጻናት አስከሬን ማንነት አልታወቀም ።
የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ "አደጋው ልብን የሚሰብር” ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ንፁሀን ልጆቻቸውን ላጡ ወላጆች የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እየገለፅኩኝ ይህን ታላቅ ሀዘን ለመሸከም ፈጣሪ ብርታትን እንዲሰጣቸው እለምናለሁ” ሲሉ መጽናናትን ተመኝተዋል።
የግዛቱ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ብራጄሽ ፓታክ በየካቲት ወር በሆስፒታሉ የደህንነት ግምገማ መካሄዱን እና ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ የእሳት አደጋ መከላከል ፍተሻ ተደርጎ እንደነበር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
የመንግስት ባለስልጣናት ለሟች ቤተሰቦች 500 ሺህ ሩፒ (5,900 ዶላር) ካሳ እንደሚከፈላቸው አስታውቀዋል።
በህንድ በስድስት ወራት ውስጥ አዲስ የተወለዱ ህፃናት በእሳት አደጋ ሲሞቱ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
በግንቦት ወር በደልሂ በሚገኘው የግል የሕፃናት ህክምና ተቋም ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ስድስት ሕፃናት መሞታቸው ይታወሳል፡፡