የፔንታጎንን የ80 አመት ክብር የነጠቀው የህንድ ግዙፍ ቢሮ
በጉጃራት ግዛት ሱራት ከተማ የተገነባውና ዘጠኝ ህንጻዎችን ያስተሳሰረው የንግድ ማዕከል 4 ሺህ 700 ቢሮዎች አሉት
130 አሳንስሮች የተገጠሙለት የንግድ ማዕከል የአልማዝና ጌጣጌጦች ግብይት ይፈጸምበታል
የህንዷ ሱራት ከተማ የአለማችን ግዙፍ ቢሮ ገንብታለች፤ የ80 አመታት የፔንታጎን ክብረወሰንም ተሰብሯል።
የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የአለማችን ግዙፍ ህንጻ ሲባል ቆይቷል።
በቨርጂኒያ አርሊንግተን የሚገኘው ፔንታጎን በ14 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው።
በህንድ ጉጃራት ግዛት ሱራት ከተማ የተገነባው የንግድ ማዕከል ግን ከፔንታጎን በ5 ሺህ 109 ስኩዌር ሜትር የሚበልጥ ነው ተብሏል።
ዘጠኝ ባለ15 ፎቅ ህንጻዎችን እርስ በርስ ያስተሳሰረው የ"ሱራት ዳይመንድ ቡርስ" 4 ሺህ 700 ቢሮዎችን አካቷል።
ለ5 ሺህ ተሽከርካሪዎች እና 10 ሺህ ሞተር ሳይክሎችን የሚይዝ ማቆሚያ ያዘጋጀው ግዙፍ ቢሮ 10 ሺህ ሰራተኞች ይኖሩታል ተብሏል።
ህንጻዎቹን የሚያገናኙ 130 ግዙፍ አሳንስሮች እንደተገጠሙለትም ግንባታውን ያከናወነው ሞርፖጀነሲስ የተሰኘ ኩባንያ አስታውቋል።
የንግድ ማዕከሉ ከፔንታጎን መብለጡ ብቻ ሳይሆን የአየር ንብረት እና ዘላቂ ልማት ሃሳብን ባገናዘበ መልኩ መገንባቱ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል የሞርፖጀነሲስ ኩባንያ መስራች ሶናሊ ራስቶጂ።
ማዕከሉ የአለማችን ግዙፍ የአልማዝ እና ጌጣጌጦች መገበያያ እንደሚሆን ተገልጿል።
የህንዷ ሱራት ከአለማችን የአልማዝ ምርት 90 በመቶው የሚቀነባበርባት ከተማ ናት። ዘርፉ ለ800 ሺህ ህንዳውያን የስራ እድል የፈጠረ መሆኑን የሚጠቅሰው ኦዲቲ ሴንትራል፥ ግዙፉ የገበያ ማዕከል አምራቾችና ገዥዎችን ከመላው አለም ለማገናኘት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ዘግቧል።
የሱራት የአልማዝ መገበያያ ማዕከል 32 ቢሊየን የህንድ ሩፒ (388 ሚሊየን ዶላር) ወጪ ተደርጎበታል።
አንድ ሰው ከዘጠኙ ባለ15 ፎቅ ህንጻዎች በአንዱ ጣሪያ ላይ ለመድረስ በአማካይ ስድስት ደቂቃዎች ብቻ ይበቁታል የተባለ ሲሆን፥ በአንድ ጊዜ ከ65 ሺህ በላይ ሰዎችን እንደሚያስተናግድም ተገልጿል።