ሽንፈትን አምኖ ለመቀበል ብርታት ያስፈልጋል የሚሉት እኝህ ፖለቲከኛ በቅርቡ በሚካሄደው የህንድ ምርጫ ላይ ለ239ኛ ጊዜ እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል
በ238 ምርጫ ላይ ተሳትፈው ሁሉንም የተሸነፉት ፖለቲከኛ
ፓድ ማራጃን በመባል የሚታወቁት ሕንዳዊ የ65 ዓመት እድሜ ያላቸው አዛውንት ሲሆኑ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በ238 ምርጫዎች ላይ ተወዳድረዋል፡፡
በተወዳደሩባቸው ሁሉም ምርጫዎች ላይ ሽንፈት ያስተናገዱት እኝህ ፖለቲከኛ “የምርጫ ንጉስ” የሚል ቅጽል ስምም በሀገሬው ሰው ወጥቶላቸዋል፡፡
በሕንዷ ሜቱር በተሰኘችው ከተማ የሚኖሩት እኝህ ፖለቲከኛ አንድ ቀን በምርጫ አሸንፌ ተመራጭ እሆን ይሆናል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል፡፡
ፖለቲከኛው ካደረጋቸው 238 የምርጫ ውድድሮች ውስጥ በፈረንጆቹ 2011 ላይ ያገኙት 6 ሺህ 273 ድምጽ በማምጣት ሁለተኛ የሆኑበት የምርጫ ውጤት በታሪካቸው ከፍተኛው የተባለ ሲሆን በወቅቱ አንደኛ የነበረው ተወዳዳሪ 75 ሺህ ድምጽ አግኝቶ ነበር፡፡
እኝህ ፖለቲከኛ ከሰሞኑ ከሕንድ ብዙሃን መገናኛዎች ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የምርጫ ውጤትን አሜን ብሎ ለመቀበል ብርታት እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
ፖለቲከኛው ለ239ኛ ጊዜም በቅርቡ በሚካሄደው የሕንድ ጠቅላላ ምርጫ ላይ እንደሚወዳደሩ መናገራቸው ትኩረት ስበዋል፡፡
ባለፉት 30 ዓመታት በተካሄዱ ምርጫዎች ላይ ለመመዝገብ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘባቸውን ወጪ ማድረጋቸውንም እኝህ ፖለቲከኛ ተናግረዋል፡፡
44 ቀናትን በመፍጀት የዓለማችን ውዱ ምርጫ የሚባለው የሕንድ ምርጫ ከ15 ቀናት በኋላ የሚጀመር ሲሆን 970 ሚሊዮን ዜጎች ድምጽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡