6 ሳምንታት በፈጀው ምርጫ የጠቅላይ ሚንስትር ናሪንድራ ሞዲ ፓርቲ ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት አግኝቷል
የአለም ውዱ ምርጫ የተባለው የህንድ አጠቃላይ ምርጫ የመጨረሻ ዙር በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በዚህኛው ዙር ድምጽ ለመስጠት ብቁ ከሆኑ 970 ሚሊየን ዜጎች መካከል 100 ሚሊየን መራጮች የሚሳተፉበት ሲሆን ላለፉት 6 ሳምንታት ሲካሄድ ቆይቷል።
በመላ ሀገሪቱ በ57 የምርጫ ክልሎች እየተከናወነ በሚገኝው ምርጫ ከ8300 በላይ እጩዎች እየተፎካከሩ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚንስትር ናሪንድራ ሞዲ የሚያሸንፉ ከሆነ ከሀገሪቱ የመጀመርያ ጠቅላይ ሚንስትር ጃዋሃራል ንሁሩ ቀጥሎ ለረጅም ግዜ በስልጣን ላይ የቆዩ መሪ ይሆናሉ።
እስካሁን ያሉ የምርጫ ውጤቶች የሞዲ ፓርቲ ባሃራቲያ ጃናታ (ቢጄ) ፓርቲ እየመራ እንደሚገኝ ሲያመላክቱ ኮንገረስ ፓርቲ ደግሞ ሌላኛው ከፍተኛ ድምጽ ያገኘ ፓርቲ መሆኑን ተጠቁሟል።
በምርጫው ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት የተሰጣቸው የ73 ዓመቱ ሞዲ ሀይማኖት መር የሆኑ ማህበረሰብ ህጎችንም አስቀራለሁ ብለዋል። እነዚህ ህጎች የጋብቻ እና ፍቺ ሁኔታ የንብረት ክፍፍል እንዲሆም ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች የሚዳኙበት እንደሆነ ይታወቃል።
ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን እየተወዳደደሩ የሚገኙት ሞዲ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ሲቀሰቅሱ ሰንብተዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ ድጋሚ የሚመረጡ ከሆነ በ2047 ሀገሪቱን ካደጉ ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡
በርግጥ ሞዲ በኢኮኖሚው ረገድ ያላቸው ሪከርድ ደካማ የሚባል አይደለም ህንድ ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት መካከል በ5ተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው በእርሳቸው የስልጣን ዘመን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ በኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻቸውም በርካታ ደጋፊዎችም አሏቸው፡፡
በአንጻሩ አስተዳደራቸው 14 በመቶ የሀገሪቱን ህዝብ ይሸፍናሉ የተባሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ማስቆም አልቻለም በሚል ይተቻል፡፡
የሂንዱ እምነት ተከታይ ናቸው የሚባሉት ሞዲ በመንግስት እና በሀይማኖት መካከል መኖር የሚገባውን ልዩነት የጠበቀ አስተዳደደር የላቸውም በሚል የሚነቅፏቸው ጥቂት አይደሉም፡፡
ይህን ክፍተት ደግሞ የኮንግረስ ፓርቲ ተቀናቃኛቸው ራውል ጋንዲ በሚገባ ተጠቅመውበታል፡፡ ራውል በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ባለፉት አመታት ተደጋጋሚ ጥቃት በሚያስተናግዱ የሙስሊም መንደሮች በማቅናት ቅስቀሳ ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡
የ1.4 ቢልየን ህዝብ ባለቤት የሆነችው ህንድ ኢኮኖሚዋ በግዝፈቱ በደረጃ ከሚጠሩት መካከል ቢሆንም አሁንም ግን በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ባለቤት ናት፡፡
ፍትሀዊ የሀብት ክፍል ፣ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ውድነት እንዲሁም የስራ እድል ፈጠራ በህንዳዊያን ዘንድ አንገብጋቢ ከሆኑ ጥያቄዎች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡
ሁለት እና ሶስት የትምህርት ድግሪ ያላቸው ህንዳዊያን በሀገር ውስጥ ስራ ማግኝት ባለመቻላቸው በተለያዩ ሀገራት ተሰደው ይገኛሉ፣ የኮንግረስ ፓርቲም በነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ በቅስቀሳዎቹ ላይ አስተጋብቷል፡፡
1.2ትሪልዮን ሩቢ ወይም 14.4 ቢልየን ዶላር የወጣበት የህንድ አጠቃላይ ምርጫ የመጨረሻው ዙር ዛሬ በመካሄድ ላይ ይገኛል የድምጽ ቆጠራ እና የመጨረሻው የምርጫ ውጤት በመጪው ማክሰኞ የሚገለጽ ይሆናል።