ሕንድ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካሽሚርን በተመለከተ የሰጡት ሃሳብ እንዳስቆጣት ገለጸች
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሕንድን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል
ሚኒስትር ዋንግ ይ ከሕንዱ አቻቸው ጋር ይገናኛሉ ተብሏል
አወዛጋቢ በሆነው የካሽሚር ግዛት ዙሪያ አስተያየት የሰጡት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሕንድ በኩል ውግዘት ደረሰባቸው፡፡
ካሽር ሕንድን እና ፓኪስታንን የሚወዛግብ አካባቢ ሲሆን እስካሁንም ስምምነት ያልተደረሰበት ቦታ ነው፡፡ ከሰሞኑ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ከኒውዴልሂ በኩል ትችት ተሰንዝሮባቸዋል፡፡ ትችት የተሰነዘረባቸው የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሰሞኑ ሕንድን ይጎበኛሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ የእስላሚክ ትብብር ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባደረጉት ስብሰባ ላይ ካሽሚርን በተመለከተ የሰጡት አስተያየት ነው ሕንድን ያስቆጣው ተብሏል፡፡
በፓኪስታን መዲና እስላማባድ የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት ዋንግ ይ ሀገራቸው በካሽሚር ጉዳይ ያላት አቋም ከእስላማዊ ሀገራት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ መግለጻቸው ነው ሕንድን ያበሳጫት፡፡
ይህንን ተከትሎም የሕንድ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የቻይናው ባለስልጣን ይህንን የማለት ምንም ስልጣን እንደሌላቸው አስታውቋል፡፡ የካሽሚር ጉዳይ የሕንድ የሀገር ቤት ስራ እንደሆነም ነው ኒውዴልሂ የገለጸችው፡፡ የቻይናው ሚኒስትር በጃሙ እና ካሽሚር ላይ የሰጡት አስተያየት ተቀባይነት እንደሌለውም ነው ሕንድ የገለጸችው፡፡
ትችት የተሰነዘረባቸው የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሰሞኑ ሕንድን ይጎበኛሉ ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን ሕንድ እና ቻይና ጦርነት ከገጠሙበት 2020 በኋላ የመጀመሪያው ነው፡፡
ዋንግ ይ ከሕንዱ አቻቸው ጃይሻንካር እና ከሀገሪቱ ብሐየራዊ የደህንነት አማካሪ አጂት ዶቫል ጋር እንደሚገናኙም ተገልጿል፡፡