ሕንድ፤ ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር የመፍታቱ ኃላፊነት የራሷ መሆኑን ገለጸች
በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ አለመግባባት ውስጥ የገቡት ሶስቱ ሀገራት ተጠቃሚ በሚያደርጋቸው መልኩ ችግሮችን እንዲፈቱም ጠይቃለች
ሕንድ ከብሪታኒያ ቅኝ አገዛዝ ነጻነቷን የተቀዳጀችበት 75ኛ ዓመት አዲስ አበባ በሚገኘው የሀገሪቱ ኤምባሲ ተከብሯል
ኢትዮጵያውያን የገጠሟቸውን ችግሮች የመፍታቱ ኃላፊነት የራሳቸው መሆኑን እንደምታምን ሕንድ አስታወቀች፡፡
በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ልክ እንደማንኛውም ሉዓላዊ ሀገር ሁሉ ኢትዮጵያም የገጠማትንና የሚገጥማትን ችግር የመፍታቱ ኃላፊነት የራሷ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ፤ የተሻለውን የማድረግ እና የወደፊቱን የመወሰን ስልጣን በራሷ እጅ ላይ ያለ መሆኑንም አምባሳደሩ አንስተዋል። ሕንድ ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር በራሷ እንደምትፈታው ሙሉ እምነት እንዳላት ተናግረዋል።
ሕንድ ከብሪታኒያ ቅኝ አገዛዝ ነጻነቷን የተቀዳጀችበት 75 ዓመት አዲስ አበባ በሚገኘው የሕንድ ኤምባሲ ተከብሯል።
በዚሁ ዝግጅት ላይ አል ዐይን ስለሕንድ እና ኢትዮጵያ ወዳጅነት የጠየቃቸው ዲፕሎማቱ፤ አዲስ አበባ እና ኒውዴልሂ ያላቸውን ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ፤ ሕንድ ነጻነቷን እ.አ.አ በ1947 ባገኘች ማግስት የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመረች ቀዳሚ ሀገር መሆኗንም ዲፕሎማቱ ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያለው ችግርም በራሳቸው በኢትዮጵያውያን አቅም እንደሚፈታም ያነሱት ዲፕሎማቱ ሁሉንም ነገር በኢትዮጵያውን የሚፈታ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለውን ግድብ በተመለከተ አስተያየት የሰጡት አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ፤ ዓባይ ወንዝ በኢትዮጵያ፤ ናይል ደግሞ በሱዳን እና ግብጽ ለዘመናት መኖሩ የሚታወቅ እንደሆነ አንስተዋል።
በወንዙ ዳርቻ ላይ ሰዎች በሰላም ሲኖሩ እንደነበር የገለጹት አምባሳደሩ፤ በግድቡ ዙሪያ አለመግባባት ውስጥ የገቡት ሶስቱ ሀገራት ተጠቃሚ በሚያደርጋቸው መልኩ ችግሮችን እንዲፈቱም ጠይቀዋል፡፡
ሕንድ ከኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላት ገልጸው በግድቡ ዙሪያ ያላግባባ ያለ ነገር ካለ ሶስቱም ቁጭ ብለው ሊፈቱ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ፤ 617 የሕንድ ኩባንያዎች የተመዘገቡ ሲሆን፤ ለ75 ሺህ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን በኢትዮጵያ የሕንድ ኤምባሲ አስታውቋል።
ሕንድ የኢትዮጵያ አራተኛዋ የንግድ አጋር ስትሆን፤ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩ በርካታ ሕንዳውያንም በአዲስ አበባ እና በሌሎች ቦታዎች ይኖራሉ።