የሕንድ ጦር አዛዥ በእስራኤል ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው
ሕንድ እና እስራኤል በወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ከሳምንት በፊት አድርገዋል
ጄነራል ማኖጅ ሙኩንድ ከ2019 ወዲህ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን ነው በእስራኤል በማድረግ ላይ ያሉት
የሕንድ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ማኖጅ ሙኩንድ ናራቫኔ በእስራኤል ጉብኝት እያደረጉ ነው፡፡
ወታደራዊ መሪው በእስራኤል ቆይታቸው ከሀገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል የተባለ ሲሆን የኤታማዦር ሹሙ ጉብኝት የሕንድ እና የእስራኤልን ወታደራዊ ትብብር እንደሚያጠናክር ተገልጿል፡፡
ጄነራል ማኖጅ ሙኩንድ ናራቫኔ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ከሆኑ ከአውሮፓውያን 2019 ወዲህ በእስራኤል ጉብኝት ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው ነው፡፡
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌፍተናንት ጄነራል አቪቭ ኮሃቪ በሀገራቸው ጉብኝት ላይ ያሉትን የሕንድ አቻቸውን ዛሬ እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡
የሕንድ መከላከያ ሰራዊት ኤታማዦር ሹምም በእስራኤል መከላከያ ኃይል የምድር ኃይል ዋና መስሪያ ቤትን ይጎበኛሉ እንደ ጄሩሳሌም ፖስት ዘገባ ከሆነ፡፡
ጀሩሳሌም ፖስት የሁለቱ ሀገራት ጦር አዛዦች ወታደራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ውይይቶችን እንደሚያደርጉ የሕንድ ጦርን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ጄነራል ማኖጅ ሙኩንድ ናራቫኔ ወደ እስራኤል ከመምጣታቸው ቀደም ብሎ የሕንድ መከላከያ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር አጃይ ኩማር በእስራኤል ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ከእስራኤል አቻቸው ጋር ውይይት ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ወታደራዊ ቦታዎችን መጎብኘታቸው ተገልጿል፡፡
ባለፈው ሳምንት እስራኤል እና ሕንድ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና በመሳሰሉት ወታደራዊ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ሥምምነት አድርገው ነበረ፡፡