ህወሃት የተመሰረተበትን 45ተኛ አመት የድርጅቱ አባላት እና ደጋፊዎች በተገኙበት በመቀሌ ስቴዲየም አክብሯል
ህወሃት የተመሰረተበትን 45ኛ አመት በርካታ የድርጅቱ አባላት እና ደጋፊዎች በተገኙበት በመቀሌ ስቴዲየም አክብሯል
ህወሃት ኢትዮጵያን ከ27 አመታት በላይ በግንባርነት ሲመራ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህዴግ) እንደ ፓርቲ ህልውናውን ካጣና ከፈረሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመሰረተበትን በዓል አክብሯል፡፡
የኢህአዴግ መስራች አባል የነበሩት ሶስት ፓርቲዎች ማለትም የደቡብ፣የኦሮሚያና የአማራ ክልል ተወካይ ፓርቲዎች ኢህአዴግ እንዲፈርስና እንዲዋሀድ ሲወስኑ በተቃራኒው ህወሃት ከውህደቱ ራሱን አግልሏል፤ አካሄዱም አፋራሽ ነው በሚል አቋሙ እስካሁን እንደጸና ይገኛል፡፡
ሌሎች የግንባሩ አባላት በመዋሀድ “የብልጽግና ፓርቲ” ሲመሰርቱ ህወሃት የያዘውን መስመር እንደማይቀይር ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
በዓሉ ህወሃት የተመሰረተበት 45ኛ አመት ሲሆን በዘንድሮው በዓል ላይ የገዥው የ“ብልጽግና ፓርቲ” ተወካዮች አልተገኙም፡፡
ነገር ግን ከህወሓት ጋር አብሮ መስራት እንደሚፈልጉ ያስታወቁ 'ፌዴራሊስት ኃይሎች' ተገኝተዋል፡፡ ከአፋር ከደቡብ ና ከሌሎችም የሃገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ተጋባዦችም ተሳትፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ፕሬዘዳንት ተቀዳሚ ሚፍት ሀጂ ኡመር ኢድሪስ እንዲሁም ከሱዳም ሰከላ ግዛት የመጡ የልኡክ ቡድን አባላት በበዓሉ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
በዓሉ 'መስመራችንን እናፅና' በሚል መሪ ቃል በርካት የድርጅቱ አባላት እና ደጋፊዎች በተገኙበት በመቀሌ ስታዲየም በተለያዩ ስነስርአቶች ታጅቦ ተከብሯል፡፡
በዓሉ ላይ የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ባደረጉት ንግግር “የትግራይ ህዝብ ከአድዋ በፊትም ሆነ በኋላ የሀገር ነጻነትና ሉዓላዊነት እንዲከበር ትልቅ መስዋዕትነት ከፍሏል”፤ ሰለሆነም "ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተገቢው መንገድ ተረድተን አዲስ ውሳኔ የምንወስንበት ታሪካዊ ቀን ነው” ብለዋል፡፡
የትግራይ ህዝብ ”የበለጠ ተጠቅሟል“ በሚል ”ጥቃት እየደረሰበት እንደሚገኝና አባረናቸዋል እየተባለም እንደሚነገርም“ የተናገሩት ዶ/ር ደብረጽዮን ይህ ሊቆም አለበለዚያም ሊቀየር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
”በአሁን ሰዓት ፈርቶ መኖር የመከባበር መንገድ እንጂ የልመና አይደለም“ ያሉም ሲሆን ለእኩልነት ታግሏል ያሉት የትግራይ ህዝብ “ከዚህ በኋላ የአንድን ብሄር የበላይነት” እንደማይቀበል ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ታግሎ ያረጋገጠው መብት እጁ ላይ” እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ደብረጽዮን ”የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሻክር፤ እንዲነጠል፤ እንዲንበረከክና አንገት እንዲደፋ ለማድረግ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመሆን ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል“ ብለዋል፡፡
በመጨረሻ የስልጣን ዘመኑ ላይ የሚገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውክልና ጊዜው ሳይጠናቀቅ ታሪክ እንዲሰራ ዶ/ር ደብረጽዮን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“መሪዎች ባለው የውጭ ጣልቃ ገብነት ምክንያት በትግራይ ህዝብና በሃገር ላይ እያደረጉ ያሉትን ጸረ ህዝብ፤ ጸረ ሃገር ንግግር በይፋ ኮንኑ፤ አውግዙ፡፡ ወይ ደግሞ ፤ትግራይ ራሷን የቻለች ሃገር ናት ብላችሁ ወስኑ፤አውጁ” ሲሉም ነው ለምክር ቤቱ ጥሪያቸውን ያቀረቡት፡፡
የሚወሰድ ”የእርምት እርምጃ“ ካለ እንዲወስድም አሳስበዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ባደረጉት ንግግር “
የትግራይና የኤርትራ ህዝብ ግንኙነትን በተመለከተም ዘርዘር ያሉ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡
ሁለቱም በአንድነት ሲታገሉ እንደነበረ ባስታወሰ ንግግራቸው ከዚህ በኋላ ቂምና ቁርሾ ቀርቶ ሰላም እንዲሰፍን የጠየቁ ሲሆን “ይህን በዚች እለት ዘግተን ለማለፍ ዝግጁ መሆናችንን ልናሳውቅ እንወዳለን“ ብለዋል፡፡
መሪዎች ይቅርና መንግስታትም ፈራሾች መሆናቸውን በመጠቆምም “ሰላማችንን ለማደፍረስ እየተሰራ ያለው የድብብቆሽ ስራ ወደ ችግር እያስገባን ስለሆነ ይህ እንዳይሆን ሁለቱም ህዝቦች ተቀራርበው ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ የሚችል ስራን መስራት” ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡