አሁንም ብጥብጥ መቆም ባለመቻሉ “ምርጫ 2012” መራዘም አለበት-የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት
አሁንም ብጥብጥ መቆም ባለመቻሉ “ምርጫ 2012” መራዘም አለበት-የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት ዛሬ በሰጠው መግለጫ በሀገሪቱ አሁንም ብጥብጥ መቆም ባለመቻሉና ይህም ምርጫ ማካሄድ ስለሚያስቸግር "ምርጫው መራዘም አለበት" የሚል ዉሳኔ እንዳሳለፈ አስታውቋል፡፡
ምክርቤቱ ብዙ ውይይት ከተደረገ በኋላ በሃገሪቱ ባለው የጸጥታ ችግር፣ ብዙ ፖለቲካ ፓርቲዎች ገና ወደ ሃገር ውስጥ ከገቡ አጭር ጊዜ መሆኑ፣ መራጩና ተመራጩ በሚገባ ባለመገናኘታቸውና በሌሎችም ጉዳዮችን ከግምት በማስገባት በ2012 ዓ.ም ሊደረግ የነበረው ምርጫ እንዲራዘም ተወስኗል ብሏል፡፡
በውይይቱ ላይ ከተገኙት ፓርቲዎች መካከል 41 የሚሆኑት ፓርቲዎች ምርጫው እንዲራዘም፣ 6 ፓርቲዎች ምርጫው እንዲካሄድና 5 ደግሞ ድምጽ አለመስጠታቸውን ነው ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡
“ምርጫም ሆነ ፓርቲ ከሃገር አይበልጥም” ያለው ምክር ቤቱ ምርጫው ባለመካሄዱ ከሚመጣው ችግር ይልቅ ምርጫው ተካሂዶ የሚመጣው መዘዝ ይበልጣልም ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ የህልውና ፈተና እንደገጠማት፣ አሁንም ብጥብጥ መኖሩንና በዚህም ምክንያት ምርጫ ማድረግ አስቸጋሪ ነው ያለው ምክርቤቱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የሃይማት አባቶች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ባህላዊ መሪዎችና ሌሎችም ለሃገራዊ አንድነት ቅድሚያ በመስጠት እንዲሰሩ ምክርቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በህገመንግስቱ መሰረት ምርጫ 2012 በተያዘው ዓመት መካሄድ ያለበት ቢሆንም፤ ፓርቲዎች በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫው ይራዘም፤ የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚል አቋም የሚያራምዱ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ቀሪዎቹ ፓርቲዎች ደግሞ ምርጫው በተቀመጠለት የጊዜ ሰሊዳ መሰረት መካሄድ አለበት ይላሉ፡፡