የምዕራባውያንን ማዕቀብ ሩሲያን ይበልጥ አጠንክሯታል - ፑቲን
ፕሬዝዳንቱ ሀገራት የምዕራባውያንን ማዕቀብ ለማለፍ ከዶላር ውጪ በገንዘባቸው እንዲገበያዩ ጠይቀዋል
የሻንጋይ ትብብር ድርጅት ጉባኤ በበይነ መረብ ተካሂዷል
ሩሲያ የምዕራባውያኑን ማዕቀብ መቃወሟን እንደምትቀጥል ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ የሻንጋይ ትብብር ድርጅት ጉባኤ በበይነ መረብ ሲካሄድ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ማዕቀቦች ሞስኮን ይበልጥ እንዳጠነከሯት ነው የገለጹት።
“ሩሲያ ሁሉንም የምዕራባውያኑን ማዕቀብ፣ ጫና እና ጸብ አጫሪነት በመመከት ታይቶ የማይታወቅ እድገት እያስመዘገበች ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
በዋግነር ከተሞከረው አመጽ በኋላ ከሀገራት መሪዎች ጋር የተወያዩት ፑቲን፥ በወቅቱ ድጋፋቸውን ላሳዩ ሀገራት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሩሲያ የሀገራቱን ማዕቀብ ለማለፍ ከተጠቀመችባቸው ዘዴዎች መካከል እንደ ቻይና ካሉ ግዙፍ ኢኮኖሚ ከገነቡ ሀገራት ጋር ከዶላር ውጪ መገበያየት መጀመሯ በአበይት ይጠቀሳል።
ሞስኮ እና ቤጂንግ 80 በመቶ የንግድ ልውውጣቸውን በሩብል እና ዩዋን ማድረጋቸውን በመጥቀስም የሻንጋይ ትብብር ድርጅት አባል ሀገራትም ይህንኑ አካሄድ እንዲከተሉ ጠይቀዋል።
የበይነ መረብ ጉባኤውን የመራችው ህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፥ የትብብሩ አባል ሀገራት የንግድ ግንኙነት ሊያድግ እንደሚገባ መናገራቸውን ሬውተርስ አስነብቧል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ በበኩላቸው የቀጠናዊ ሰላምና ደህንነት ትብብር እንዲጠናከር ነው መልዕክት ያስተላለፉት።
ቻይና እና ሩሲያ የምዕራባውያንን ጫና ለመመከት ከሌሎች አራት የማዕከላዊ እስያ ሀገራት ጋር በመሆን በፈረንጆቹ 2001 የሻንጋይ ትብብር ድርጅትን ማቋቋማቸ ይታወሳል፤ ህንድ እና ፓኪስታን ደግሞ በ2017 ድርጅቱን ተቀላቅለዋል።
የሻንጋይ ትብብር ድርጅት የአለማችን 40 ከመቶ ህዝብ እና 20 ከመቶ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ቢይዝም እንደ ቡድን 20 እና ብሪክስ ስብስብ ተጽዕኖው ሊጎላ አልቻለም።
ኢራንም በዚህ አመት የድርጅቱ ሙሉ አባል ትሆናለች የተባለ ሲሆን፥ ከህንድ ውጪ ከምዕራባውያን ጋር የተኳረፉ ሀገራት የተሰባሰቡበት ነው።