ዩክሬን የሩሲያዋን ኩርስክ ክልል በሚሳኤሎች እና ድሮኖች ደበደበች
ሩሲያ 117 የዩክሬን ድሮኖችን መትታ በመጣል የዩክሬን ወታደሮች የሚገኙባቸውን አካባቢዎች በጄት እየደበደበች መሆኑን አስታውቃለች
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የዩክሬን ጦር ሩሲያ መግባት ፑቲንን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል ብለዋል
ዩክሬን የሩሲያዋን ኩርስክ በሚሳኤሎች እና ድሮኖች በመደብደብ ይበልጥ ዘልቃ እየገባች መሆኑን አስታወቀች።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በኩርስክ ያለው ሁኔታ መረጋጋቱን ቢገልጹም የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ወታደሮቻቸው ወደ ሩሲያ ግዛት ዘልቀው መግባታቸውን መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
ዜለንስኪ የሀገሪቱን ጦር ለሚመሩ ጀነራሎች በዘመቻው ቀጣይ ሂደት ዙሪያ አዲስ እቅድ እንዲያወጡ ማዘዛቸውንም ነው የገለጹት።
ሩሲያ ዛሬ ማለዳ ባወጣችው መግለጫ በኩርስክ፣ ቮሮኔዥ እና ቤልጎሮድ ክልሎች 117 የዩክሬን ድሮኖችን መትታ መጣሏን አስታውቃለች።
የሀገሪቱ ኤስዩ-34 ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችም የዩክሬን ወታደሮች በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ድብደባ መፈጸማቸውን መግለጿን ሬውተርስ ዘግቧል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴርም ሆነ ዩክሬን በድሮን እና ሚሳኤል ድብደባው የደረሰውን የጉዳት መጠን አልጠቀሱም።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሩሲያ ላይ በተፈጸመው ወረራ ዙሪያ ከዩክሬን ጋር በተከታታይ መረጃ እየተለዋወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
የዩክሬን ጦር ወደ ሩሲያ ዘልቆ መግባት የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ ነው ማለታቸውንም ዋይትሃውስ ያወጣው መግለጫ ያመላክታል።
ዋሽንግተን ዩክሬን በሩሲያ ከፈጸመችው ወረራ ጋር በተያያዘ እጄ የለበትም ብትልም ሞስኮ ግን ምዕራባውያን የኬቭ አጋሮች ስለወረራው አስቀድመው እንደሚያውቁ ገልጻለች።
ዩክሬን ከባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ በሩሲያ በፈጸመችው ወረራ ከ200 ሺህ በላይ ሩሲያውያን ተፈናቅለዋል፤ ለቀናት በቀጠለው ውጊያም በንጹሃን ህይወትና ንብረት ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱ ነው ሲዘገብ የቆየው።
ፕሬዝዳንት ፑቲን የሀገራቸው ጦር በፍጥነት “ወራሪው”ን ሃይል ጠራርጎ እንዲያስወጣ ቢያዝም የዩክሬን ጦር ወደፊት ገሰገሰ እንጂ እስካሁን አላፈገፈገም።
ኬቭ በትናንትናው እለትም ከሩሲያ ግዛት ውስጥ 100 ሺህ ሄክታሩን ተቆጣጥሬታለሁ ማለቷ ይታወሳል።
የሁለት አመቱን ጦርነት ሜዳ ወደ ሩሲያ ወስጀዋለሁ ያለችው ዩክሬን፥ ሩሲያ ተገዳ ወደ ድርድር እንድትመጣ ለማድረግ ዘመቻውን መክፈቷ ይነገራል።
ክሬምሊን ግን ከወረረን አካል ጋር አንደራደርም፤ ከምዕራባውያን ይሁንታን ላገኘው የዩክሬን ወረራ ፈጣን ምላሽ እንሰጣለን የሚል ምላሽ ሰጥቷል።