ከ154 በላይ ክሩዝ ሚሳኤሎች እና የኒዩክሌር አረሮችን መሸከም የምትችለው መርከብ በሲዊዝ ቦይ አቅራቢያ ደርሳለች
የአሜሪካ መካላከያ ሚኒስቴር (ፔንታጎን) የሀገሪቱ ኒዩክሌር ተሸካሚ ባህር ሰርጓጅ መርከብ መካከለኛው ምስራቅ መድረሷን ገልጿል።
የኦሃዩ ምድብ የባህር ሰርጓጅ መርከቧ ስያሜ ባይጠቀስም የኒዩክሌር አረር ተሸካሚዋ መርከብ በቀጠናው የመገኘት ጉዳይ ባልተለመደ መልኩ በይፋ ተገልጿል።
የኒዩክሌር ተሸካሚ መርከቦቿን እንቅስቃሴ በሚስጢር ስትይዝ የቆየችው አሜሪካ፥ ባህር ሰርጓጅ ግዙፍ መርከቧ ከካይሮ በሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ በስዊዝ ቦይ አቅራቢያ መድረሷን ይፋ አድርጋለች።
የአሜሪካ ባህር ሀይል አራት የኦሃዩ ምድብ ባህር ሰርጓጅ ኒዩክሌር ተሸካሚ መርከቦች ያሉት ሲሆን መርከቦቹ 154 ቶማሃውክ ክሩዝ ሚሳኤሎችን መያዝ ይችላሉ።
እያንዳንዱ ክሩዝ ሚሳኤልም 1 ሺህ ፓውንድ የሚመዝንና ከፍተኛ ፍንዳታ ሊያስከትል የሚችል ፈንጂ መሸከም የሚችል መሆኑንም ሲኤንኤን ዘግቧል።
ዩኤስኤስ ፍሎሪዳ የተሰኘችው ኒዩክሌር ተሸካሚ ባህር ሰርጓጅ መርከብ በፈረንጆቹ 2011 በሊቢያ 100 ቶማሃውክ ክሩዝ ሚሳኤሎችን በመተኮስ ያደረሰችው ውድመትም የመርከቧ አደገኛነት ማሳያ ተደርጎ ይነሳል።
ለ77 ቀናት በባህር ላይ መቆየት የሚችሉት የኦሃዩ ምድብ የጦር መርከቦች እስከ 7 ሺህ 400 ኪሎሜትር የሚምዘገዘጉ ባለስቲክ ሚሳኤሎች ታጥቀዋል፤ 80 የኒዩክሌር አረሮችንም መሸከም ይችላሉ።
አሜሪካ "አይዘንሀወር" እና "ጀራልድ ፎርድ" የተሰኙ የጦር አውሮፕላኖችን የሚሸከሙ መርከቦችንና ከ2 ሺህ በላይ ወታደሮችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ መላኳ ይታወሳል።
በትናንትናው እለትም ኒዩክሌር ተሸካሚ ባህር ሰርጓጅ መርከቧን የላከችውም የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ወደ ቀጠናው እንዳይሳፋፋ ለማድረግ በማለም ነው ብሏል ፔንታጎን።
እርምጃው ኢራን እና እንደ ሄዝቦላህ ያሉ የምታስታጥቃቸው ቡድኖች በጦርነቱ እጃቸውን ከማስገባት እንዲቆጠቡ ለማስጠንቀቅ ጭምር የተወሰደ መሆኑ ተገልጿል።
በሶሪያና ኢራቅ በሚገኙ ወታደራዊ ጣቢያዎቿ ላይ የድሮን እና ሚሳኤል ጥቃት የተፈፀመባት ዋሽንግተን ወታደሮቿን ለመጠበቅ ፈጣን እርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቃለች።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሊዩድ ኦስቲን "የእስራኤሌና ሃማስን ጦርነት ለማስፋፋት የሚሞክር የትኛውም ሀገር ወይም ሀይል አንታገስም" ማለታቸውም ይታወሳል።