ሩሲያ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ተመንን ለደገፉ ሀገራት ነዳጅ እንዳትሸጥ የሚከለክል ህግ አወጣች
የቡድን ሰባት ሀገራት የሩሲያ ነዳጅ በበርሜል ከ60 ሺህ ዶላር በላይ እንዳይሸጥ ወስነው ነበር
ሩሲያ የቡድን ሰባት ሀገራት ተመንን ተከትሎ ነዳጅ ማምረቷን ቀንሳለች
ሩሲያ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ተመንን ለደገፉ ሀገራት ነዳጅ እንዳትሸጥ የሚከለክል ህግ አወጣች።
ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ ጦርነት ካመሩ 10 ወራትን ያስቆጠሩ ሲሆን ይህ ጦርነት በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል።
ሞስኮ በዩክሬን የጀመረችውን ጦርነት እንድታቆም በርካታ ጫናዎች ከአሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት ገጥሟታል።
ከጫናዎቹ መካከልም ሩሲያ ነዳጇን ለዓለም ገበያ እንዳታቀርብ ማዕቀብ መጣል ዋነኛው ሲሆን ይህ ማዕቀብ የታሰበውን ያህል ለውጥ እንዳላመጣ ይገለጻል።
የቡድን ሰባት ሀገራት ሩሲያ ነዳጅ በበርሜል ከ60 ሺህ ዶላር በላይ እንዳይሸጥ ከአንድ ወር በፊት እገዳ ጥለዋል።
የቡድን ሰባት ሀገራት እገዳ ዓላማው ሩሲያ በበጀት እጥረት ምክንያት በዩክሬን የጀመረችውን ጦርነት እንድታቆም ለማድረግ ያለመ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
ይሁንና የቡድን ሰባት ሀገራት በሩሲያ ነዳጅ ላይ የዋጋ ተመን ማስቀመጣቸውን ተከትሎ የዓለም ነዳጅ ዋጋ በበርሜል ወደ 80 ሺህ ዶላር ከፍ ብሏል።
ሩሲያ በበኩሏ የነዳጅ ተመን ዋጋ ላስቀመጡ እና ህጉን ተቀብለው ለሚያስፈጽሙ ሀገራት ነዳጅ ላለመሸጥ የሚከለክል ህግ አውጥታለች።
የሩሲያ ፕሬዝዳንቱ ቭላድሚር ፑቲን ይህ ህግ እንዲተገበር በፊርማቸው ማጽደቃቸውን ራሺያ ቱዴይ ዘግቧል።
የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ በሩሲያ ጋዝ ላይ ማዕቀብ መጣላቸውን ተከትሎ በአውሮፓ ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት አጋጥሟል።
የነዳጅ እጥረቱን ተከትሎም መንግስታቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲያደርግላቸው አውሮፓዊያን በሰላማዊ ሰልፍ እና በስራ ማቆም አድማ ጫና በመፍጠር ላይ ናቸው።