አሜሪካና ሳዑዲ አረቢያ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያን ለማረጋጋት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሳዑዲ አረቢያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል
ዋሽንግተንና ሪያድ የጋራ ጠላታቸው ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳትታጠቅ ለማስቆም ተስማምተዋል
አሜሪካና ሳዑዲ አረቢያ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያን ለማረጋጋት ለመስራት መስማማታቸው ተሰምቷል።
በሳዑዲ አረቢያ ጉብኝት ላይ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከሳዑዲ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር አርብ ዕለት ከተወያዩ በኋላ የሳዑዲ መንግሥት የዜና ወኪል ባወጣው የጋራ መግለጫ፣ ዋሽንግተን እና ሪያድ በተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ላይ ለመስራት መስማማታቸውን አስታውቋል።
በዚህም አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ እንዲሁም ሚዛናዊ የዓለም የነዳጅ ገበያዎችን ለመደገፍ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
ሁለቱ ሀገራት በአለም አቀፍ የነዳጅ እና የኃይል ገበያ ላይ በአጭር እና በረጅም እቅድ በማውጠት በጋራ ለመምከር እና ለመስራት መስማማታቸውም ተመላክቷል።
ዋሽንግተን እና ሪያድ የጋራ ጠላታቸው የሆነችው ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያከመታጠቅ ለማስቆም አስፈላጊ መሆኑን እና በጋራ ለመስራት መስማማታቸውንም አስታውቀዋል።
መግለጫው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አሜሪካ “የሳውዲ አረቢያን ደኅንነት እና የግዛት አንድነትን ለመደገፍ እንዲሁም የሀገሪቱን መንግስት እና ህዝብ ከውጭ አደጋዎች ለመከላከል አስፈላጊውን ድጋፍ እንምታደርግ ቁርጠኛ መሆኗን እንዳረጋገጡ ተመላክቷል።
በመካከለኛው ምስራቅ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን ከእስራኤል እና ፍልስጤም ቆይታቸው በኋላ በትናትናው እለት ሪያድ ደርሰዋል።
“የሰላም ጉዞ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የፕሬዝዳንቱ የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት፤ አሜሪካ በጊዜ ሂደት እየቀነሰ የመጣው በቀጠናው ያላትን ተጽእኖ በድጋሚ እንዲያንሰራራ ሚያደረግ ነው ተብሎለታል።