ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ባለቤታቸው በኮሮና መያዛቸውን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኮሮና መያዛቸው በቀጣዩ ምርጫ ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል?
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ባለቤታቸው ሜላኒያ ትራምፕ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን እና ራሳቸውን መለየታቸውን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
የ74 ዓመት አዛውንቱ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዕድሜ አንጻር ቫይረሱ እንደሚያሰጋቸው እየተነገረ ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ በቫይረሱ የተያዙት የ31 ዓመቱ አማካሪያቸው ሆፕ ሂክስ ቫይረሱ ከተገኘበት በኋላ ነው፡፡ ትራምፕ በቫይረሱ መያዛቸውን በገለጹበት የትዊተር ገጻቸው “በጋራ እናልፈዋለን” ብለዋል፡፡
የቅርብ አማካሪያቸው ሂክስ በበሽታው መያዛቸውን ካረጋገጡ በኋላ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ የኮቭድ -19 ምርመራ አድርገው ውጤት ሲጠብቁ እንደነበር ከገለጹ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው የራሳቸውን በቫይረሱ መያዝ ይፋ ያደረጉት፡፡
የፕሬዝዳንት ትራምፕ ሀኪም እንዳሉት ፕሬዝዳንቱ እና ቀዳማዊት እመቤት በተጠንቀቅ ከሚቆም የህክምና ቡድን ጋር በኋይት ሀውስ ራሳቸውን አግልለው ይቆያሉ፡፡
የኋይት ሀውስ ሀኪም የሆኑት ስኮት ኮንሌይ “ፕሬዚዳንቱ በማገገም ላይ ሳሉ ስራቸውን ያለማቋረጥ መወጣታቸውን እንደሚቀጥሉ እጠብቃለሁ ፤ ወደፊት በሚከሰቱ ክስተቶች ላይ ደግሞወቅታዊ መረጃዎችን አደርሳለሁ” ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለምን ያህል ጊዜ ራሳቸውን አግልለው እንደሚቆዩ ባይገለጽም የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከል ማዕከል ሰዎች በቫይረሱ ከተያዙ ለ 14 ቀናት እንዲገለሉ ይመክራል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ከ 205,000 በላይ ሰዎችን ለህልፈት የዳረገው ቫይረሱ በዋናነት ዕድሜያቸው የገፋ ሰዎችን የሚጎዳ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ፕሬዝዳንቱንም ለከፍተኛ ችግሮች የማጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ የዘ ናሺናል ዘገባ ያመለክታል፡፡
ቫይረሱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ለቫይረሱ ከፍተኛ ንቀት ሲያሳዩ የነበሩት ፕሬዛዳንት ትራምፕ ቫይረሱን ለመከላከል የሚወስዷቸው እርምጃዎች በብዙዎች ዘንድ እንዲተቹ አድርጓቸዋል፡፡
ከአንድ ወር በኋላ ለሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም የዚሁ ቫይረስ ጉዳይ አንዱ ትልቅ የምርጫ ቅስቀሳ ነጥብ ሆኗል፡፡
ከትናንት በስቲያ በተካሔደው የትራምፕ እና የዴሞክራቱ ጆ ባይደን ክርክር አንዱ አጀንዳም ይኸው ነበር፡፡ እስካሁን በአሜሪካ ቫይረሱ ህይወታቸውን ከነጠቃቸው ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች ማካከል ማስክ በማድረግ ብቻ የግማሹን ህይወት ማትረፍ ይቻል እንደነበር በማንሳት ቫይረሱ በአሜሪካ ላስከተለው ጥፋት ባይደን ትራምፕን ተጠያቂ አድርገው ተከራክረዋል፡፡ ከዚህም ጋር በማያያዝ ትራምፕን በአሜሪካ ታሪክ አሳፋሪው ፕሬዝዳንት እንደሆኑ ሲገልጹም ነበር፡፡
አሁን ደግሞ ይህ አስከፊ ቫይረስ ፕሬዝዳንቱን ራሳቸውን ማግኘቱ ለባይደን ቀጣይ ቅስቀሳ ትልቅ ድል ሲሆን ፕሬዝዳንቱን ደግሞ ነጥብ ሊያስጥላቸው እንደሚችል ብዙዎች እምነታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
ከአሜሪካውያን የተሰበሰቡ አስተያየቶች አብዛኛው አሜሪካዊ በፕሬዝዳንቲ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) አያያዝ ደስተኛ እንዳልሆኑ ያሳያል፡፡
የትራምፕ ደጋፊዎችም ፕሬዝዳንቱ በተለምዶ የምርጫው ዉጤት የሚወሰንባቸው ድምጾች በሚገኙባቸው እንደ ሚቺጋን ፣ ኦሀዮ ፣ ፔንሲልቫኒያ እና ዊስኮንሲን ባሉ ግዛቶች ፕሬዝዳንቱ ድጋፍ እንዳያጡ በመስጋት ላይ ናቸው፡፡ ትራምፕ የ 2016ቱን ምርጫም ያሸነፉት በነዚህ ግዛቶች ባገኟቸው ድምጾች ነው፡፡ ምንም እንኳን አሁን ላይ በነዚህ ወሳኝ ግዛቶች ተቀራራቢ ድጋፍ ቢኖራቸውም ጆ ባይደን በግዛቶቹ ትኩረት አድርገው እየሰሩ ነው፡፡