ቫይረሱ ከዚህ በኋላ ከፕሬዝዳንቱ ወደ ሌሎች ሰዎች እንደማይተላለፍ ሀኪማቸው አስታውቀዋል
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኮሮና ከተያዙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ህዝብ ፊት ቀረቡ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በትናንትናው ዕለት በደጋፊዎቻቸው ፊት የምርጫ ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡
የኋይት ሀውስ ሀኪሙ ዶ/ር ሲን ኮንሌይ ፕሬዝዳንቱ በቤተ መንግሥቱ ጊቢ የምርጫ ቅስቀሳ ንግግር ካደረጉ ከ7 ሰዓት በኋላ በሰጡት መግለጫ ቫይረሱ ፕሬዝዳንቱ ቫይረሱን ወደሌሎች ግለሰቦች የማያስተላልፉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡
ይሁንና እንደ ሮይተርስ ዘገባ የኮንሌይ መግለጫ ፕሬዝዳንቱ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን ስለማመልከቱ የታወቀ ነገር የለም፡፡
ኮሮና እስካሁን በአሜሪካ ከ7.9 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን ከነዚህም ከ219 ሺ በላይ ሰዎች መሞታቸውን የዎርልዶሜትርስ መረጃ ያሳያል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና አስተዳደራቸው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አያያዛቸው እንዲሁም በማስክ አጠቃቀም ቸልተኝነታቸው ሰፊ ወቀሳዎችን አስተናግደዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ በትንሹ 11 የቅርብ ሰዎቻቸውም በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡
የኮሮና ህክምናቸውን አድርገው ወደ ኋይት ሀውስ ከተመለሱ በኋላ ፣ ትናንት ቅዳሜ ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ በህዝብ ፊት ባደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ ንግግራቸውም ወቅት ፕሬዝዳንቱ ማስክ አላደረጉም፡፡
ርቀታቸውን ሳይጠብቁ ለተሰበሰቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር ጥሩ ስሜት እየተሰማቸው እንደሆነ በመግለጽ “ሶሻሊስት” እና “ኮሚዩኒስት” በማለት ዴሞክራቶችን ተችተዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ በትናንቱ የምርጫ ቅስቀሳቸው ከቀድሞው አንጻር አጭር ንግግር ነው ያደረጉት፡፡